በፍርድ ቤቶች ሙስናን ጨምሮ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጀ

92

 ሰኔ 11/2014 (ኢዜአ) በፍርድ ቤቶች ሙስናን ጨምሮ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂ መዘጋጀቱን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስታወቀ፡፡

የፌደራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት በበኩሉ ተገልጋዮች በፍትህ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች በሚመለከት ጥናት ማካሄዱን ገልጿል፡፡

የዜጎች የሰብዓዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አስተዳደራዊና ተቋማዊ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ከሚሰሩ ተቋማት መካከል ግንባር ቀደሞቹ የፍትሕ ተቋማት መሆናቸው ይታወቃል።

በፍትሕ ተቋማት ማለትም በፍርድ ቤቶች፣ በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ተቋማት የሚታዩ የአስተዳደር፣ የሙስናና የስነ-ምግባር ችግሮች ዜጎች ፍትሕ እንዳያገኙ በማድረግ ሀገርን ለከፋ ቀውስ ይዳርጋሉ።

በዚህ ረገድ የፌደራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ፤ በፍትሕ ተቋማት በተገልጋዮች ላይ የሚደርሱትን ችግሮች መለየትና የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከለውጡ ወዲህ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በፍርድ ቤቶች እንዲሁም በፖሊስ ተቋማት የተገኙ ውጤቶችና የታዩ ችግሮችን የሚዳስስ ጥናት ተካሄዷል ነው ያሉት፡፡

የጥናቱ ውጤትም በመጪው ሰኞ ይፋ እንደሚያደርግና  ከፍትሕ ተቋማት ጋር እንደሚወያዩበት ገልጸዋል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ብዙ ጥያቄዎች እንደሚነሱ ጠቅሰው፤ የሙያ ስነ-ምግባር አለማክበርና ሙስና ከፍተኛ ቅሬታ የሚነሳባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ በትግበራ ሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ስትራቴጂው በፍርድ ቤቶች ከሙስና ተግባር ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።

በሙስናና ብልሹ አሰራር ላይ የተሰማሩ ዳኞች ላይ እርምጃ ለመውሰድም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የማጥራት ስራ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም