አምራች ኃይሉን በክህሎት፣ በእውቀትና ሥልጠና በማገዝ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሥራ ባህል መለወጥ ይገባል

33

ሰኔ 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ አምራች ኃይል በክህሎት፣ በእውቀትና ሥልጠና በማገዝ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሥራ ባህል ለመለወጥ መሥራት እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን በማድረግ የሚካሄደው ''ጉሚ በለል'' 23ኛው ዙር የውይይት መድረክ " የሥራ ባህል እና ማኅበረሰባዊ እሴቶች " በሚል ርዕሰ ጉዳይ ተካሂዷል።

በውይይቱም ድህነትን ለማሸነፍና ራስን ለመቻል ዘላቂነት ያለው ጠንካራ የሥራ ባህል ሊኖር እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

እንደ አገር ለረዥም ጊዜ ያለውን ደካማ የሥራ ባህል ለመቀየር በእውቀት እና በክህሎት የዳበረ ማኅበረሰብ መፍጠር ተገቢ መሆኑም ተገልጿል፡፡    

የውይይቱን መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የኦሮሚያ ሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አደም ከማል፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ብልጽግናን ለማምጣትና የተሻለ የሕብረተሰብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሥራ ባህላችንን መለወጥ አለብን ብለዋል።

በተለይ በወጣቶች ዘንድ ዝቅ ብሎ ከታች ሥራ መጀመር አለመፈለግና የጠባቂነት ባህል በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ማምጣት የሚችል የሰው ኃይል አቅም መኖሩን ጠቅሰው፤ ይህን ኃይል በክህሎትና ሥልጠና በመደገፍ ጠንካራ የሥራ ባህል ማስፈን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

በሕብረተሰቡ ዘንድ የእርስ በርስ ትስስርን በማጎልበት በጋራ ሰርቶ የሚለወጥ ማኅበረሰብ መገንባት እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

"አፍሮ ዩኒቨርሳል" የተሰኘ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አህመድ አቡበከር በበኩላቸው፤ የሥራ ባህልን መቀየር ድህነትን ለማሸነፍ ወሳኝ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡    

የበለጸጉት አገራት እድገት ምስጢር ጠንካራ የሥራ ባህል መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም የሥራ ባህላችንን መቀየር ለነገ የሚተው ተግባር መሆን የለበትም ነው ያሉት፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም አገርን መለወጥ የሚቻለው ጠንካራ የሥራ ባህል በመገንባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጠንካራ የሥራ ባህልን በመገንባት ረገድ መንግሥት የመሪነት ሚናውን መወጣት እንዳለበት ጠቅሰው፤ በተለይ መገናኛ ብዙኃን የሕብረተሰቡን የሥራ ባህል በመገንባት ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ሕብረተሰቡም ከሥራ ጠባቂነት ወደ ሥራ ፈጣሪነት ለመሸጋገር ቁርጠኛ ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት  ማብራሪያ እንደ አገር መሻሻል ካለባቸው ጉዳዮች አንዱ የሥራ ባህል መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም