21 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከምዝበራ እንዲድን ተደርጓል

52

አሶሳ፣  ሰኔ 11 / 2014 (ኢዜአ ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስነምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን 21 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከምዝበራ ማዳኑን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽነር መንግስቱ ላሎ ለኢዜአ እንደገለጹት ኮሚሽኑ በ2014 በጀት ዓመት 339 የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች ደርሰውታል፡፡

ጥቆማዎችን መሠረት በማድረግ በክልሉ በሚገኙ መንግስታዊ ተቋማት ላይ ባካሄደው ክትትልና ማጣራት ከፋይናንስ መመሪያ እና ደንብ ውጪ ያለአግባብ ሊመዘበር የነበረ 17 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ማዳኑን አስታውቀዋል፡፡

በተቋማቱ የፋይናንስ ደንብና መመሪያ ያልጠበቁ የንብረት ግዥ ሂደቶችና ጨረታ አሸንፈው በገቡት ውል መሰረት  ደረጃውን የጠበቀ ቁሳቁስ ያላቀረቡ አካላት ውላቸው እንዲሰረዝ በማድረግ ገንዘቡን ከምዝበራ ማዳን እንደተቻለ አመልክተዋል ።

እንዲሁም ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የኦዲት ግኝት ወደ መንግስት ካዝና እንዲመለስ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ በክልሉ ለሚገኙ ለ95 ሺህ ተማሪዎች ጨምሮ ከ200 ሺህ በላይ  ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናና ትምህርት መሰጠቱን ተናግረዋል ።

በተጨማሪም በ40 መንግስታዊ ተቋማት ላይ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ የ10ሩ ተጠናቆ ተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጣቸውን እና ሌሎች ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮቻቸው እንዲያሻሽሉ ምክረ ሃሳብ ከማቅረብ ጀምሮ ችግሩን አስቀድሞ የመከላከል ስራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በሃሰተኛ የትምህርት እና በሌሎች ሰነዶች ላይም ጠንካራ ክትትል መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

አመራሩን ጨምሮ 1ሺህ 665 የመንግስት ሠራተኞች ሃብታቸውን እንዲያስመዘግቡ እና እንዲያሳድሱ መደረጉን ጠቁመው ሃብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ባልሆኑ ሁለት አመራሮች ላይ ክስ መመስረቱን አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሚያደርገው ሙስናን የመከላከል ሂደት  የክልሉ መንግስት እገዛ የሚበረታታ መሆኑን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ በየደረጃው የተጠናከረ መዋቅር የሌለው መሆኑ፣ የጸጥታ ችግር፣ ህብረተሰቡ የሚሰጣቸውን ጥቆማዎች በምስክርነት አለማስደገፍ በበጀት ዓመቱ ሙስናን በመከላከል ሂደት የገጠመው አስቸጋሪ ሁኔታዎች መሆናቸውን ኮሚሽነር መንግስቱ ጠቅሰዋል፡፡

ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙሉዓለም አድማሱ እንዳሉት ሙስናን በሚገባ መከላከል የህግ የበላይነት እና ፍትሃዊነትን ለማስፈን ወሳኝ ነው፡፡

"ህብረተሰቡ ልጆቹን በመልካም ስነምግባር አንጾ ከማሳደግ ጀምሮ መንግስት ችግሩን ለመቀረፍ የሚያደርገውን ጥረት በሃላፊነት መደገፍ ይገባዋል" ብለዋል፡፡

 "የሙስናን ችግር በዘላቂነት ለመቀነስ ተተኪው ትውልድ ጠንካራ ስራ ይጠብቀናል" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ሰለሞን ካሳ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም