ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የክልሎች ሁለንተናዊ ድጋፍ ወሳኝነት አለው

74

ሰኔ 10 ቀን 2014 ( ኢዜአ)ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ሠላማዊ ሁኔታ ለማሸጋገር ተስፋ ለተጣለበት ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት የክልሎች ሁለንተናዊ ድጋፍ ወሳኝነት እንዳለው ተመላከተ።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስትና ከባለድርሻ አካት ጋር ዛሬ በአሶሳ ከተማ ውይይት አድርጓል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት ኮሚሽኑ ህብረተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀውን ሀገራዊ ምክክር ለማስጀመር እየሰራ ነው፡፡

''ሀገራዊ ምክክሩን አካታች ማድረግ ወሳኝ ነው'' ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ይህንኑ መሰረት በማድረግ ከክልሎች ጋር የትውውቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ጠንካራ የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራት አስፈላጊ ነው መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነር ሂሩት፤ክልሎች ለኮሚሽኑ የእውቀት፣የሀሳብ፣ የበጀት እና ሌለችንም ሁለንተናዊ ድጋፎች እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ኮሚሽነር መላኩ ገብረማርያም በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክር አድርገው ሳይሳካቸው የቀሩ ሀገራት ዋነኛ ችግራቸው ለውይይት አጀንዳ ተቀርጾ ለህብረተሰቡ በመሰጠቱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክሩ መሰል ችግር እንዳያገጥመው ህብረተሰቡ ራሱ የመወያያ ሃሳቦችን በነጻነት እንዲያፈልቅ ለማድረግ ኮሚሽኑ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በየወረዳው ያለውን ህብረተሰብ በምክክሩ ለማካተት እንደሚሰራ ጠቁመው፤በቅርቡ የምክክሩን ጉዳይ የሚከታተሉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች በየክልሉ ይመደባሉ ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው ኮሚሽኑ የያዘው ዓላማ ኢትዮጵያዊያንን የጋራ አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ ሀገራዊ መግባባት የማምጣት አቅም እንዳለው አመልክተው፤ የክልሉ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሀገር ሽማግሌ አቶ አልከድር አህመድ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ባህላዊ እሴቶችን መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ገታ ጋጋ በበኩላቸው ''ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የጋራ ተጠቃሚነትን ማስቀደም አለብን'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም