ለጤና ተቋማት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያና መድሐኒት ተሰራጭቷል - ኢዜአ አማርኛ
ለጤና ተቋማት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያና መድሐኒት ተሰራጭቷል

ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ)በመጠናቀቅ ላይ ባለው የበጀት ዓመት ለሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ስር ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያና መድሐኒት መሰራጨቱን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የሀገሪቷን የጤና ተቋማት የመድሐኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አሰራር ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገልጸዋል።
ዘመናዊ አሰራርን የተከተለ የህክምና መሳሪያና የመድሐኒት አቅርቦት ለማረጋገጥ የሚያስችል የሀገራችን መድሐኒት አምራቾች፣የህክምና መሳሪያና መድሐኒት አስመጭ ድርጅቶች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደገለጹት ለሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ስር ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና መሳሪያዎችና መድሐኒቶች መሰራጨታቸውንም ተናግረዋል።
በተለይ በህልውና ዘመቻ ወቅት በአሸባሪው ህወሃት የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና አግልግሎት እንዲጀምሩ በማድረግ በኩል የተሻለ ስራ ተሰርቷል፡፡
በህክምና መሳሪያዎች፣በመድሐኒትና በሌሎች የህክምና ቁሳቁሶች የማደራጀት ስራ ተሰርቷል።
ይሁን እንጂ አሁንም የመድሐኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አሰራሩን ከማዘመን ጀምሮ ሰፊ ስራዎች ከፌዴራል ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የሚጠብቁን ቀዳሚ ተግባር ናቸው ብለዋል።
በአማራና በአፋር ክልል 42 ሆስፒታሎችን መልሶ በማደራጀት ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉን የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው በዚህም ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ በህልውና ዘመቻ ወቅት በአሸባሪው ህወሃት በህክምና ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመቋቋም በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የዘርፉ ሙያተኞች፣የመድሐኒት አምራቾችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው ብለዋል።
በተመሳሳይ በኮሮናና በድርቅ ምክንያት ዜጎች በመድሐኒትና የህክምና መሳሪያዎች እጥረት እንዳይጎዱ ያልተቋረጠ ርብርብ መደረጉን አመልክተዋል።
በጤና ተቋማት ፈጣን አገልግሎት ለመስጠትና የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ ዘመናዊ የመድሐኒትና የህክምና መሳሪያ አቅርቦት አሰራር ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
የመድሐኒት ብክነት፣የአያያዝና የዘመናዊ አሰራር ጉድለት፣የክምችት ቦታዎችና የህክምና መሳሪያዎች ጥገና ማዕከላት እጥረት በጤና ተቋማት የሚታዩና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እንቅፋት የሆኑ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዘንድሮ ዓመት ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት የህክምና መርጃ መሳሪያዎች በተለይ የኤክስሬይ፣ራዲዮሎጅና ሌሎች መሳሪያዎች ጥገና መደረጉን ተናግረዋል።