በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ "ራስ ጠቆሮ" ጥብቅ ደን ላይ ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ ማጥፋት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ "ራስ ጠቆሮ" ጥብቅ ደን ላይ ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ ማጥፋት ተችሏል
ሰኔ 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ "ራስ ጠቆሮ" ጥብቅ ደን ላይ ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ ከህብረተሰቡ ጋር በተደረገ ርብርብ ማጥፋት መቻሉን የወረዳው አካባቢና ደን ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የአምባሰል ወረዳ አካባቢና ደን ጥበቃ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ ወይዘሮ ዚነት መሃመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰኔ 6 ቀን 2014 ዓ/ም እኩለ ሌሊት በወረዳው 016 ቀበሌ "ራስ ጠቆሮ" ጥብቅ ደን የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ቆይቷል።
አካባቢው ተራራ ከመሆኑ ባለፈ በደኑ ተቀጣጣይ ሳርና እንጨቶች መኖራቸው ለማጥፋት ከፍተኛ ጫና ቢያሳድርም ከህብረተሰቡ ጋር ሌት ተቀን በተደረገ ርብርብ እሳቱን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በተነሳው የሰደድ እሳት ቃጠሎም ከ4 ሄክታር የሚበልጥ የደኑ ክፍል ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቁመው፤በውስጡ የነበሩ እንሰሳትና እጽዋት ላይ ጭምር ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
"ራስ ጠቆሮ" ጥብቅ ደን ከ8 ሄክታር መሬት በላይ ስፋት ያለው ሲሆን የተጎዳው ደን መልሶ እንዲያገግም በቀጣይ ክረምት የተጠናከረ የችግኝ ተከላና መንከባከብ ስራ ይከናወናል።
ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ በተራ ደኑን ለመጠበቅ ጭምር ቃል ገብተዋል ብለዋል፡፡
በወረዳው የ016 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይመር ታደሰ በሰጡት አስተያየት በደኑ ላይ የተከሰተውን እሳት በርብርብ ማጥፋት ተችሏል፡፡
ጥብቅ ደኑ መኖሩ ጎርፍ ከመከላከሉ ባለፈ አካባቢውን የአፈር ለምነት እንዲጠብቅ አድርጎ ነበር ያሉት አቶ ይመር መልሶ እንዲያገግም የሚጠበቅብንን እናደርጋለን ሲሉ ገልፀዋል።
በጥብቅ ደኑ ጅብ፣ድኩላ፣ሚዳቆ፣ ነብር፣ሰሳ፣ ቀበሮና ሌሎች የዱር እንሰሳትን ጨምሮ ዝግባ፣ ግራር፣ ጽድ ወይራ፣ ብሳናና ሌሎች እጽዋቶችም ይገኙል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ