የሃይማኖት አባቶች በአዲሱ ዓመት ህብረተሰቡ አንድነትና መቻቻልን እንዲያጎለብት ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች በአዲሱ ዓመት ህብረተሰቡ አንድነትና መቻቻልን እንዲያጎለብት ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 የሃይማኖት አባቶች በአዲሱ ዓመት ህብረተሰቡ አንድነትና መቻቻልን እንዲያጎለብት ጥሪ አቀረቡ። የሃይማኖት አባቶች ጥሪውን ያቀረቡት 'በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር' በሚል በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ እየተካሄደ በሚገኘው የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የእስልምና፣ የካቶሊክና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች ቤተክርስቲያን አባቶች ባስተላለፉት መልዕክት የዘንድሮው አዲስ ዓመት የምናከብረው ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ በምትገኝበት ወቅት መሆኑ፣ በቅራኔ ውስጥ የነበሩ በርካታ የፖለቲካ ቡድኖች እርቅ ያወረዱበትና ታስረው የነበሩ ወገኖች ከእስር የለተቀቁበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። ይህ ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥላቻን በማስወገድ መቻቻልን በማጎልበት ለአንድነት መትጋት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።