ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች ነው

131

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 10/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ዳይሬክተር ኤልያስ መላኩ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካል ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ስትሆን፤ በዚህም ከቀጣናው አገራት ጋር በልማትና በተለያዩ መስኮች በትብብር እየሰራች ነው፡፡

በተለይ ቀጣናውን በመሰረተ-ልማት በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊ ትብብሮችን ለማጠናከር እየሰራች ሲሆን፤ የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር መስመር ሥራና የኢትዮ-ኬንያ የአስፋልት መንገድ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ትስስሮችን ይበልጥ በማጠናከር በአህጉሪቷ ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት በትብብር እየሰራች መሆኑ ይጠቀሳል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ጉዳይ ዳይሬክተር ኤልያስ መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ በማጠናከር ለአህጉሪቷ አገሮች የእርስ በርስ ትብብር የበኩሏን ሚና እየተወጣች ነው፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት የዚሁ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በናይጄሪያ ያደረጉት ጉብኝትን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ተገናኝተው የሀገራቱን የኢኮኖሚ ትስስር የሚያጠናክሩ ስምምነቶችን ስለማድረጋቸው አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይም ከሴኔጋል፣ አይቬሪኮስት፣ ቶጎና ሌሎችም ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ትስስር በመፍጠር ጠንካራ አህጉር ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት ሰፊ የበረራ ሽፋን እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህም ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ያላትን ትስስር ለማጠናከር ያግዛል ነው ያሉት፡፡

መሰል ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የተናገሩት፡፡

በአገራቱ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን አማካኝነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡               

ኢትዮጵያ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጠንካራ ትስስር እየፈጠረች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ሥራ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ለማስፋት በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ተናግረዋል፡፡

ይህም አህጉሪቷን ወደ ተሻለ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም