ቀጥታ፡

የሐዋሳ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል እየተካሄደ ያለው በምርምር የተደገፈ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ዘላቂ ጥቅም አስገኝቷል

ሐዋሳ ሰኔ 10/2014 (ኢዜአ)፡ የሐዋሳ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል እየተከናወነ ያለው በጥናትና ምርምር የተደገፈ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለአካባቢው ማህበረሰብ ዘላቂ ጥቅም እያስገኘ መሆኑን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በየኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ሙሉጌታ ዳዲ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራ ባሻገር የአካባቢውን ማህብረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮችን እያካሄደ ነው።

 የሐዋሳ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ወደ ሐይቁ ደለል ይዘው የሚመጡ በዙሪያው ካሉ ተፋሰሶች መካከል በሲዳማ ክልል ቦሪቻ ወረዳ ይርባ ዱባንቾ ቀበሌ የሚገኘውን ጥልቀት ያለው የቦሮቦር ሥፍራ ለማከምና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አካባቢውን በተለመደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዘዴ ማከም ስለማይቻል ዩኒቨርሲቲው የሐይቁን ህልውና ለመታደግ በጥናትና ምርምር የተደገፈ አዲስ ቴክኖሎጂ ለማፍለቅ መቻሉን አስታውቀዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት  በ12 ሄክታር ላይ አዲሱን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ በማድረግ ሥፍራውን ለማከም ጥረት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ቴክኖሎጂው የምህንድስናን ጥበብ ከሥነ ምህዳር ጋር ያዛመደ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ሙሉጌታ፤ ከትላልቅ ግንባታዎች ይልቅ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ እንጨት ፣ ቀርከሃና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመጠቀም የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ መሰራቱን አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂው የድንጋይ ግንባታን ሊሸከሙ በማይችሉ የቦሮቦር ሥፍራዎች ላይ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ለተጀመረው የተፋሰስ ልማትና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ውጤታማነት እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂው  በአይምሯዊ ንብረትነት እንዲመዘገብ መደረጉን ጠቅሰው፤በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም ጥቅም ላይ እንዲውል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ፕሮጀክቱ የሐዋሳን ሐይቅ ከደለል ከመከላከል ባለፈ የቦታውን ሥነ-ምህዳር በማከም የአካባቢው ማህበረሰብ ተፈጥሮን እየተንከባከበ በዘላቂነት እንዲጠቀምበት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ተናግረዋል።

በማህበር ተደራጅተው ቦታውን በኃላፊነት እየጠበቁ መጠቀም ከጀመሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ንጉሴ ዶንጋቶ አካባቢው በጎርፍ ተሸርሽሮ ከመጎዳቱ በፊት በዛፎችና ደን የተሞላ እንደነበር አስታውሰዋል።

''ለአሥር ዓመታት አካባቢው ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ በጎርፍ በመቦርቦሩ  ከዛሬ ነገ የእርሻ መሬታችንን ልናጣ እንችላለን የሚል ሥጋት ተደቅኖብን ነበር'' ብለዋል።

 ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተግባራዊ ያደረገው ቴክኖሎጂ ችግሩን እንዲቀርፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።

''ተራቁቶ የነበረው አካባቢያቸው  ወደ ቀድሞ ገጽታው በመመለሱ ተስፋችን ለምልሟል'' ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቂ ሥልጠና ከሰጣቸው በኋላ በቦታው ላይ ንብ ማነብ የሚያስችላቸውን  ግብዓቶች እንዳሟላላቸው ተናግረዋል።

ሌላዋ ተጠቃሚ ወይዘሮ ሂሩት ሂጊሶ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ሥፍራው እጅግ ገደላማ በመሆኑ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጅውን ተጠቅሞ በሰራው ሥራ በአካባቢው አስደሳች ለውጥ መታየቱን ጠቁመዋል።

በሥፍራው ካለሙት የመኖ ሣር ለከብቶቻቸው በመውሰድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 የሐዋሳ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከሚከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ባሻገር ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል የአካባቢ ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽታዬ ዩሙራ ናቸው።

''በሐይቁ ዙሪያ ባሉ ቦሪቻ ፣ ሀቤላ እና ሀዋሳ ዙሪያ ወረዳዎች ላይ የአርሶ አደሩን ማሳ ጨምሮ 600 ሄክታር የሚሆን መሬት ላይ ውጤታማ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራ ማከናወን ችለናል'' ብለዋል።

ወደ ሐይቁ የሚገባ ደለልም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተው፤ የዩኒቨርሲቲው የጥናትና ምርምር ውጤት የሆነውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተሞክሮ በሌሎች የክልሉ ቆላማ ወረዳዎች ላይ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሐይቁን በደለል ከመሞላትና ከብክለትም ለመታደግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችና ሌሎች ጥናት ላይ የተመሰረቱ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል ።

የሐዋሳ ሀይቅ 1 ሺህ 432 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ያህል ስፋት እንዳለው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም