ቱሪዝም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት የሚያበረክተውን ድርሻ ለማሳደግ በትብብር መሰራት ይገባል-የቱሪዝም ሚኒስትሯ

161

ሀዋሳ ሰኔ 09/2014 (ኢዜአ).ኢትዮጵያ ያላት የቱሪዝም ሀብት ለሃገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ አስገነዘቡ።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሀዋሳ ያዘጋጀው “ ስለ ኢትዮጵያ ” የተሰኘ የፎቶግራፍ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ተካሂዷል።

ሚኒስትሯ አውደ ርዕይና የፓናል ውይይት ሲከፍቱ  እንደተናገሩት ቱሪዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነው።

በተለይ በሥራ ዕድል ፈጠራ ፣ በማህበራዊና አካባቢያዊ ዕድገት ውስጥ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ነው ያስገነዘቡት።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር  በ2019 ከአጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ የነበረው ድርሻ 10 በመቶ እንደነበር ጠቅሰው፣ ለ334 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ መፍጠሩን ለአብነት አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ  ካላት እምቅ የቱሪዝም አቅምና መዳረሻዎች አንፃር እያገኘቸው ያለው ጥቅም  እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

መንግስት ነባራዊ ሁኔታውን ለመቀየርና ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ተገቢውን ድርሻ እንዲይዝ አስቻይ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ነው ያሉት  ሚኒስትሯ፤  የግሉ ዘርፍ ፣ መገናኛ ብዙኃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ መንግስት ለዘርፉ ዕድገት ምቹ መደላድል ለመፍጠር ፖሊሲዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ባለፈ ቱሪዝምን ከማህበራዊ ዘርፍ ወደ ኢኮኖሚ ዘርፍ ማሸጋገር ችሏል።

ከአምስት የኢኮኖሚ አውታሮች አንዱ የሆነውን የቱሪዝምን ዘርፍ በከፍተኛ ትኩረት በመምራት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቁልፍ አካል እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአሁኑ  ወቅት በመንግስት እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ሀብቶችን ማዕከል ያደረጉና ለዘርፉ ዕድገት መሠረት እንደሚጥሉ ጠቅሰዋል።

የፓናል ውይይቱን የመሩት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ክልሉ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ ሳቢ የሆኑና እንደ ሀገር የተነደፈውን ስትራቴጂ ዕውን ሊያደርጉ የሚችሉ ሀብቶች በክልሉ እንዳሉ ጠቁመዋል።

በተለይ የሰው ልጆች ሠላም ፣ ደህንነት ፣ ፍቅርና አብሮነት ለቱሪዝም ዕድገት አስቻይ ሁኔታዎች በመሆናቸው ሁሌም ተጠብቀው ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

ዘርፉን በሚፈለግበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ በትብብርና በአብሮነት መንፈስ መስራት እንደሚያስፈልግ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሀገራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት “ ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትቀጥላለች ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚያዘጋጀው “ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘው መድረክ ለኢትዮጵያ አንድነትና ገፅታ ግንባታ የሚያበረክተው አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የባህል ቱሪዝም እንቅስቃሴን አስመልክተው የመነሻ ፅሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሀት ቱሪዝም የአድናቆት ገበያ መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች እንዲከናወኑ ጠቁመዋል።

በተለይ የባህል ሀብቶችን ሥነ-ጥበባዊ እሴቶች ማጉላትና ማስተዋወቅ እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት።

በዱር እንስሳት ጥበቃና ዘላቂ ጥቅም ላይ ፅሑፍ ያቀረቡት የዘርፉ ምሁር ዶክተር ፋኑኤል ከበደ እንደ ዱር እንስሳት ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ከሰው ልጆች ህልውና ጋር መቆራኘታቸውን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ካለባቸው ተራራማ ሥፍራዎች እጅግ ሞቃታማ እስከሆነው የዳሎል ዝቅተኛ ሥፍራ ጀምሮ ብዝሃነት ያላቸው አስደናቂ የዱር እንስሳት መገኛ መሆኗን ጠቁመው፣ ይህንን ሀብት በአግባቡ መጠበቅ የሥነ-ምህዳርን ሚዛን ከመጠበቅ ባለፈ ከፍተኛ ገቢ ሊያስገኝ ይችላል ብለዋል ፡፡

ለዚህም አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ ፣ ጥቅም ላይ ማዋልና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ  ከሁሉም ባለድርሻ አካላት እንደሚጠበቅ ዶክተር ፋኑኤል አብራርተዋል።

በመርሀ-ግብሩ ማጠቃለያ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲዳምኛ ቋንቋ/“ሲዳሙ አፎ ” የተተረጎመው “አሻራ” የተሰኘ የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ የሚያመላክት መጽሐፍ ተመርቋል።

መጸሐፉን  የመረቁት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ ጌትነት ታደሰ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም