ኢዜአ እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከተማውን በአለማቀፍ ደረጃ ማስተዋወቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

82

ሰኔ 09 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የባለብዙ ሃብት ባለቤት የሆነችውን ከተማ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ እና  የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ስምምነቱን ፈርመዋል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም ከተማ የሆነችውን ሀዋሳ ለዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ከኢዜአ ጋር በጋራ መሥራቱ ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል።

ለአገሪቷ የብልጽግና ጉዞ አጋዥ የሆኑና ከተማዋ የተሻለ ገቢ የምታገኝባቸውን ፕሮጀክቶች በመንደፍ ወደ ተግባር መግባቱንም ተናግረዋል።

ከኢዜአ ጋር በትብብር ለመሥራት የተደረሰው ስምምነትም የከተማዋን የቱሪዝም ሃብት፣ የኢንቨስትመንት አማራጮችና የልማት ክንውኖችን ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀዋሳ ከተማ ያላትን እምቅ ሃብት በማስተዋወቅ እድገቷ እንዲፋጠንና ተጠቃሚነቷ እንዲያድግ የሚዲያው ሚና የማይተካ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት /ኢዜአ/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ፤ ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር የተደረገው ስምምነት ለውጤታማ ሥራዎችና የጋራ ፍላጎቶች ስኬት መልካም እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ሀዋሳ ከተማ ከቱሪዝም መዳረሻነቷ ባለፈ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ ተባብረውና ተከባብረው የሚኖርባት ውብ ከተማ መሆኗን ጠቅሰው፤ ኢዜአ ይህን የሚያጎሉ ሥራዎችን ተደራሽ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአገር ውስጥ ቋንቋዎች ከሚያሰራጫቸው ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎች በተጨማሪ በውጭ ቋንቋዎችም ፈጣንና ትክክለኛ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ ይታወቃል።

በተለይም በእንግሊዝኛ፣ በአረብኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋዎች የሚያሰራጫቸው ዜናዎች ለተቀረው ዓለም በቀላሉ ተደራሽ ለመሆን ያስችለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም