ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ማብራሪያ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በአግባቡ እንድንረዳ አድርጎናል

ድሬዳዋ፤ ሰኔ 09/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በአግባቡ እንዲረዱ እንዳስቻላቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከትላንት በስትያ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ማብራሪያ አስመልክቶ ነው ነዋሪዎቹ አስተያየታቸውን የሰጡት።

የከተማው ነዋሪ አቶ ደምሴ አቡላ እንዳሉት መንግስት በመላው አገሪቱ ህግን ለማስከበርና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እየሰራቸው ያሉ ተግባራት ለዜጎች ደህንነት ዋስትና እየሰጡ ናቸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያዎች ህዝብን ከመደነጋገር ያላቀቁና በርካታ የልማት ስራዎች መሰራታቸውን በግልጽ እንድንረዳ አስችሎናል ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ደምሴ እንዳሉት ከመንግስት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥና የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የድርሻችንን መወጣት አለብን ፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት አሊ አልይ "እኔም ሆንኩ ሌሎች ወጣቶች በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚለቀቁ መረጃዎችን ሣናጣራ ከመቀበል በመጠንቀቅና ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲረጋገጥ እራሳችንን ማዘጋጀት ይኖርብናል "ሲል ተናግሯል፡፡

"ባለፉት አራት አመታት የተገኘውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መክሸፋቸውን ገልፆ በቀጣይም ወጣቱ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሰለፍ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የድርሻውን መወጣት አለበት" ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ሚዲያ የሚተላለፉ የተሳሳቱ መረጃዎች በተመለከተ የሰጡት ማብራሪያ ለህብረተሰቡ ግልጸኝነትን የፈጠረና መረጃዎችን በአግባቡ መረዳትና ማጣራት እንደሚገባ መልእክት ያስተላለፈ መሆኑን የተናገረው ሌላው የከተማው ወጣት ቲጃኒ አባጅሃድ ነው።

ወጣት መኮንን ነብይ በበኩሉ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠው ማብራሪያ ጠንካራ ሀገረ-መንግስት ለመገንባት እየተደረገ ላለው ጥረት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጿል።

"ወጣቱ የመንግስት እጅ ከመጠበቅ ይልቅ የራሱን ሥራ በመፍጠርና የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የዜግነት ድርሻውን መወጣት አለበት" ሲል ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም