ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ 'በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር' በሚል በሚካሄደው አዲስ ዘመን ማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተዋል

73
አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 'በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር' በሚል በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ በሚካሄደው የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሰንደቅ ዓላማ ያለበት ካኔተራ ለብሰዋል። አሮጌውን ዓመት በመሸኘት አዲሱን ለመቀበል መንግስት ባዘጋጀው በዚህ መርሃ-ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች በመርሃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ታድመዋል። የሁለቱ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ዜጎች የዝግጅቱ ታዳሚያን ናቸው። በምሽቱ ክንዋኔ የተለያዩ የድንገቴ መርሃ-ግብሮች እንደሚኖሩ የሚጠበቅ ሲሆን ኢትዮጵያውያን በሰላም፣ በፍቅርና በይቅርታ ተደምረው  ለአንድነት እንዲተጉ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን ያዘሉ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም