የቱርኩ ቻሊክ ሆልዲንግ ኩባንያ በተፈጥሮ ጋዝና ማዳበሪያ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ

111

ሰኔ 09/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጋዝና ማዳበሪያ ዘርፍ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው የቱርኩ ቻሊክ ሆልዲንግ ኩባንያ አስታወቀ።

ኩባንያው ይዞት የመጣው የልዑካን ቡድኑ 12 አባላትን ያቀፈ ሲሆን በማዕድን ሚኒስቴር የሚገኘውን የማዕድን ጋለሪ ጎብኝቷል።

በጉብኝቱ ላይ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ፤ በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አደም መሀመድ እና ከቱርክ የመጡ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል፡፡

በወቅቱ ሀገሪቱ በማዕድን ዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም በተመለከተ የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ፤ ለልዑኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም የቱርኩ ቻሊክ ሆልዲንግ ኩባንያ በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ጋዝና ማዳበሪያ ምርት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየቱ ነው የተጠቀሰው።

ለባለሃብቶቹ አገሪቷ በማዕድን፣ በብረት፣ በተፈጥሮ ጋዝና ፔትሮሊየም ዘርፍ ያሏትን መልካም አጋጣሚዎች በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያና ገለጻ ተሰጥቷል።

የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ አገራቱ ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን ለማጠናከር በመሪዎች ደረጃ ውይይቶች ማካሄዳቸውን አመልክተው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር ቱርክ ኢስታንቡል ላይ በተካሄደ ፎረም ላይ የኢትዮጵያ ልዑክ መሳተፉን አብራርተዋል።

ከፎረሙ ጎን ለጎንም የቱርክ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከቱርክ ንግድ ሚኒስቴር ጋር ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማየትና ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ልዑኩን በማመስገን ለስኬታማነቱ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያና ቱርክ ረጅም ጊዜ የቆየ አጋርነት ያላቸው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ይህን መሰል ኢኮኖሚያዊ ትብብሮች ግንኙነቱን የበለጠ እንደሚያጠናክሩት አስረድተዋል።

የቻሊክ ሆልዲን ኩባንያ ሊቀመንበር አህመት ቻሊክ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ ሁኔታ በተመለከተ ጠቃሚ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያልተነኩና ጥቅም ላይ ያልዋሉ በርካታ ሀብቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ እነዚህን ሀብቶች ወደ ውጤት ለመቀየር የበኩላችንን ጥረት እናደርጋለን ሲሉም አክለዋል።

አገራቱ ያላቸው ግንኙነት እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው ተጨማሪ የቱርክ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል።

"የሁለቱን አገራት ህዝቦች የሚጠቅም ፕሮጀክት ላይ መሳተፍ ለእኛ ትልቅ ኩራት ነው" ያሉት ሊቀመንበሩ በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም