በሲቪል ሰርቪሱ የአሰራር ህጉን በመጣስ የትኛውንም ቡድን ይሁን ግለሰብ ለመጥቀም የሚከናወን ቅጥር የለም

157

ሰኔ 9 ቀን 2014 (ኢዜአ)በሲቪል ሰርቪሱ የአሰራር ህጉን በመጣስ የትኛውንም ቡድን ይሁን ግለሰብ ለመጥቀም ተብሎ የሚከናወን ቅጥር የለም ሲሉ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ስመኝ ውቤ ገለጹ።

የሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ ተቋማዊ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን በጠበቀ መልኩ ስራውን እየከወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከቀናት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።

በእለቱ ከምክር ቤት አባላት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ "ተረኝነት" በሚመስል መልኩ የአንድ ወገን ውክልና ገዝፎ ይታያል የሚል ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤በማብራሪያቸው የሚወራው ከእውነታው የራቀ መሆኑን በመግለጽ እውነታውን ለማወቅ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሄዶ ማረጋገጥ እንደሚቻል አመላክተው ነበር።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ከፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ስመኝ ውቤ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አንድ ሰራተኛ ገና ሲቀጠር ጀምሮ ተፈላጊ ችሎታ፣የትምህርት ደረጃንና ሌሎች ዝቅተኛ የቅጥር መስፈርት አሟልቶ የሚቀጠር መሆኑን በመግለጽ የሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ ተቋማዊ ነጻነቱን ጠብቆ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሲቪል ሰርቪስ ዘርፉ ተቋማዊ ነጻነቱንና ገለልተኝነቱን በጠበቀ መልኩ ስራውን እየከወነ መሆኑን ገልጸው የትኛውንም ቡድን ይሁን ግለሰብ ለመጥቀም ተብሎ የሚከናወን ቅጥር የለም ብለዋል።

የመንግስት ሰራተኛ ቅጥር የሚካሄደው በግልጽ ማስታወቂያ በማወዳደር እንጂ የማንም አካል ጣልቃ ገብነት የሌለበት መሆኑን አስረድተዋል።

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የ246 ሺህ የፌዴራል መንግስት ሰራተኞችን መረጃ በአግባቡ አደራጅቶ ይዟልም ነው ያሉት።በመሆኑም እውነታውን መረጃ ማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም አካል ወደ ተቋሙ መጥቶ ማረጋገጥ ይችላል ብለዋል።

የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የ22 ሚኒስቴር መስሪያ ቤትንና የ69 ተቋማት ሰራተኞችን መረጃ አድራጅቶ መያዙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም