‘’ዓመቱ በአትሌቲክስ ውድድር ጥሩ ውጤት የታየበት ነበር’’ -አምባሳደር መስፍን ቸርነት

196

ሰኔ 8 ቀን 2014(ኢዜአ) ዓመቱ በአትሌቲክስ ውድድር ጥሩ ውጤት የታየበት እንደነበር የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።

በሞሪሺየስ በተካሄደው 22 ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፈውና አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው ልዑክ ዛሬ ይፋዊ አቀባበል ከተደረገለት በኋላ ሽልማት ተበርክቶለታል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ በመርሃ ገበሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት አመቱ በአትሌቲክስ ውድድሮች ስኬታማ ውጤት የተመዘገበበት እንደነበር ገልጸዋል።

በአንዳንድ ውድድሮች ላይ አትሌቶች ከህመማቸው ጋር እየታገሉ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዐላማ ከፍ ማድረግ መቻላቸውን አስታውሰው የአትሌቶች መገለጫ የሆነውና ነባሩ የጀግንነትና የፅናት ተምሳሌት ዛሬም መቀጠሉ የሚያኮራ መሆኑን ተናግረዋል።

አትሌቶች በቅርቡ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ መንፈስ ለሌላ ድል መዘጋጀት እንዳላባቸውም አስገንዝበዋል።

በተለይ በዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና ህዝቡ ከፍተኛ ውጤት የሚጠበቁ በመሆኑ ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ በማሳሰብ በውድድሩ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ መንግስት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ አትሌቶቹ በሻምፒዮናው ያስዘመገቡት ውጤት አበረታች መሆኑን ገልጻለች።

ሀገርን መወከል ከባድ ኃላፊነት እንደሆነ በመጠቆም ከአንድ ወር በኋላ ለሚደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዝግጅት ለማድረግ ለአትሌቶች ጥሪ መደረጉን ተናግራለች።

ኢትዮጵያ በ22 ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና 4 ወርቅ፣ 6 ብር እና 4 ነሐስ በድምሩ 14 ሜዳሊያ በማግኘት 5ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቃለች።

ፌዴሬሽኑ በሻምፒዮናው ወርቅ ላመጡ አትሌቶች 40 ሺህ ብር፣ የብር ሜዳሊያ ላመጡ 25 ሺህ ብር፣ ነሐስ ላገኙ 15 ሺህ ብር የሸለመ ሲሆን በውድድሩ ዲፕሎማ ላገኙ አትሌቶች 10 ሺህ ብር ሲሸለሙ አመርቂ ተሳትፎ አድርገው ለተመለሱት የ5 ሺህ ብር ተሽልማት በርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም