በባህር ዳር ከተማ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የመሰረተ ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው

73

ባህር ዳር፤ ሰኔ 7/2014 ( (ኢዜአ) ) በባህር ዳር ከተማ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች የሚመልሱ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አስታወቁ።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በከተማው እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማትና የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በዚህ ወቅት እንዳሉት በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየተሰራ ነው።

በከተማዋ እየተገነቡ ከሚገኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶች መካከልም የ11 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም 10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ግንባታ ሥራ እየተፋጠነ መሆኑን አመልክተው፤ በከተማዋ አዲስ እየተመሰረቱ ባሉ መኖሪያ አካባቢዎችም የ28 ኪሎ ሜትር የአዲስ መንገድ ከፈታና የጠጠር ማልበስ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

በፌዴራል መንግስት በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘው አዲሱ ተለዋጭ የዓባይ ድልይና ከእሱ ጋር ተያይዞ እየተገነባ ያለው የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታም እየተፋጠነ መሆኑን ተናግረዋል።  

ከ3ኛ ወገን ነፃ ማድረግ፣ ያልተገባ የካሳ ጥያቄ፣ ካሳ ከተከፈለ በኋላ ፈጥኖ ለመነሳት ፈቃደኛ አለመሆን ለአንዳንድ ፕሮጀክቶች መጓተት ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

"ከዚህ በተጨማሪ የግንባታ እቃዎች መናር፣ ተቋራጮች በቂ ሲሚንቶ አለማግኘትና የአቅርቦት እጥረት ለፕሮጀክቶች ግንባታ ፈጥኖ አለመጠናቀቅ ተጨማሪ ምክንያቶችና አሁንም ያልተሻገርናቸው ችግሮች ናቸው" ብለዋል።

የግንባታ ግብዓት ችግሮችን ለመፍታት  የከተማ አስተዳደሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

ከጉብኚዎቹ መካከል የደቡብ ጎንደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደሰ ይርዳው በበኩላቸው፣ "በባህር ዳር ከተማ እየተገነቡ ያሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች የብልፅግና ጉዟችንን ለማሳካት ለምናደርገው ጉዞ ማሳያ ናቸው" ብለዋል።

በፌዴራል መንግስት በዓባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው አዲሱ ተለዋጭ ድልድይ ከተማዋን  ማራኪና ተመራጭ ከተማ እንደሚያደርጋት ጠቁመዋል።

"እኛም በቀጣይ በየአካባቢያችን የሚገነቡ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ለረጅም ዓመታት እንዲያገለግሉ አድርገን መገንባት እንዳለብን በጉብኝቱ ካየነው መልካም ተሞክሮ ወስደናል" ብለዋል።

የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ግንባታን በጉብኝት ወቅት መመልከታቸውን የገለጹት ደግሞ የደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብዟለም አያሌው ናቸው።

"በጉብኝቱ ያገኘነውን ተሞክሮ ወስደን በከተማችን የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመፍታት እንሰራለን" ሲሉ አስገንዝበዋል።

የደረጃ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ አፍሪካ ብረታብረት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን አያሌው በበኩላቸው፣ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጭ በ8 ወራት ውስጥ የፋብሪካው የግንባታና የማሽን ተከላ ሥራ ተጠናቆ ለስራ ዝግጁ ማድረጉን ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በሰጣቸው 44 ሺህ 180 ካሬ ሜትር ቦታ ግንባታውንና የማሽን ተከላውን በማጠናቀቅ በአጭር ጊዜ የሙከራ ምርት ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ በባህር ዳር ከተማ ስልጠና ሲከታተሉ የነበሩ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች መሳተፋቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም