የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት 10 ሺህ 400 መጻሕፍትን አበረከተ

65

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት 10 ሺህ 400 መጻሕፍትን አበረከተ።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ መጻሕፍቱን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተወካይ ዶክተር ታምራት ኃይሌ አስረክበዋል።    

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም 5 ሺህ መጻሕፍትን ያበረከተ ሲሆን የዛሬውን ጨምሮ በአጠቃላይ ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ከ15 ሺህ 400 በላይ መፃሕፍትን ነው ያበረከተው።   

ከተበረከቱ መጻሕፍት መካከል በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የታተመውና በሲዳምኛ ቋንቋ የተጻፈው አሻራ የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ንግግር አንዱ ነው።   

በመጽሐፍ መልክ የታተሙ የፎቶ ግራፍ ስብስቦች፣ ልብወለዶች፣ የታሪክና የሳይንስ መጻሕፍትም ተካተዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌትነት ታደሰ፤ መጻሕፍቱ ከሰራተኞች፣ ከድርጅቱ የቀደሞ ባልደረቦች፣ ከግል ኮሌጆችና ከግለሰቦች  የተሰበሰቡ ናቸው።  

"ጫማ በመጥረግ የሚተደደሩ ዜጎች ጭምር ያቀረብነውን ጥሪ በመቀበል መጻሕፍት የለገሱ አሉ" ያሉት  ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የላስቲክ ቤት ወጥሮ የሚኖር አንድ ዜጋም 900 መጻህፍትን መለገሱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ የበርካታ አንጋፋ ደራስያን መፍለቂያ እንደመሆኑ ለስነ ጽሑፍና ህትመት ዘርፉ ያለው አበርክቶ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመው ለቋንቋዎች እድገትም የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።

ድርጅቱ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ የአገር ውስጥና የውጭ ዜጎች የመረጃ ምንጭ ከመሆን ባለፈም ታሪክን ሰንዶ ለትውልድ ማሻገር ላይ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።  

ለሁለተኛ ጊዜ 8 ሺህ 100 መጻህፍትን ለማሰባሰብ እቅድ ተይዞ እንደነበር አስታውሰው ከእቅድ በላይ መከናወኑንም ገልጸዋል።  

ጫማ በመጥረግ ስራ የሚተዳደሩ ዜጎች መጻሕፍት መለገሳቸው አስተማሪና ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተወካይ ዶክተር ታምራት ሃይሌ፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ከመገናኛ ብዙሃን ስራው ጎን ለጎን በመጻሕፍት አበርክቶ ላይ እያከናወነ ያለው ተግባር  የሚመሰገን ነው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም መጻሕፍት በማሰባሰብ ለአብርሆት በማበርከት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም