ቀጥታ፡

በበዓሉ ለሚያጋጥም የኃይል መቆራረጥ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል---የኤሌክትሪክ አገልግሎት

ሀዋሳ ጶግሜ 5/2010 በዘመን መለወጫ በዓል የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ክስተት ሲያጋጥም አስቸኳይ መፍትሄ ለመስጠት ዝግጅት ማድረጉን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ። የአገልግሎቱ ስራ አስፈጻሚ አቶ ክንፈ ነጋሽ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በሁሉም ዲስትሪክቶች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ ቡድን ተደራጅቷል ። ሂደቱን የሚቆጣጠር ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል፡፡ "ድንገት የሚከሰቱ የኃይል መቆራረጥ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ዲስትሪክቶች በቂ ሰው ኃይልና የቁሳቁስ አደረጃጀት አድርገዋል" ብለዋል ። በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ንክኪ የሚገጥም የኃይል መቋረጥ ለመቆጣጠር ዛፍ ያለባቸው ስፍራዎችን በመለየት የመቁረጥ ስራ ተከናውኗል፡፡ የትራንሰፎርመር መቃጠል ክሰተትን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል። "በበዓላት ወቅት የኃይል ፍላጎት ይጨምራል" ያሉት ስራ አስፈጻሚው ከፍተኛ ኃይል ተጠቃሚ የሆኑ ፋብሪካዎች፣ መበየጃ ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ከዋዜማው ጀምሮ ኃይል እንዳይጠቀሙም አሳስበዋል፡፡ "ህብረተሰቡም በየቤቱ አጠቃቀሙን በማስተካከል ኃይል ሊቆጥብ ይገባል" ብለዋል። አምፖሎች፣ ምድጃዎችና ኤሌክትሪክ የሚፈልጉ መገልገልያዎችን ከተጠቀሙ በኋላ በማጥፋት በበዓል ወቅት የሚያጋጥመውን የኃይል መጨናነቅ ለመቀነስ ተጠቃሚዎች መተባባር እንዳለባቸውም  ስራ አስፈጻሚው አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም