ዩኒቨርሲቲዎች የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ግለሰቦች ሊደግፉ እንደሚገባ ተገለጸ

162

አሶሳ፤ሰኔ 07 / 2014 (ኢዜአ) ዩኒቨርሲቲዎች የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ግለሰቦች በመደገፍ የማህበረሰቡን ችግር እንዲፈቱ ማድረግ እንደሚገባቸው የትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።

“ፈጠራ ለተሻለ የማህበረሰቡ ህይወት” በሚል መሪ ሀሳብ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ሽግግር ሲምፖዚዬም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በሚኒስቴሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች አስተባባሪ ዶክተር ዱላ ቶሌራ እንደገለጹት ያደጉ ሀገራት አሁን ለደረሱበት ስልጣኔ መሠረቱ ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀማቸው ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች በየአካባቢያቸው የሚገኙ የተለያዩ የፈጠራ ሥራ  የሚያካሂዱ ግለሰቦችን መደገፍ እንደሚገባቸው አመልክተው፤ ይህም የማህበረሰቡን ችግሮች ለመፍታት አስታዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የፈጠራ ሥራን ለማበረታታና ለማውጣት የሚያስችል ፖሊሲ፣ የመመሪያ መዘጋጀቱን  ጠቁመዋል፡፡

በአሶሳ የኒቨርሲቲ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ዶክተር ሃይማኖት ዲሳሳ በበኩላቸው የኒቨርሲቲው የፈጠራ ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች ለይቶ ለማበረታታ ጥረት እያረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሲምፖዚዬሙ ለእይታ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎችን ጨምሮ በተለይ በዘር ብዜትና በግብርና ፈጠራ በሀገር አቀፍ ደረጃ አውቅና ያገኙ የፈጠራ ባለሙያዎች መኖራቸውን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለሁለተኛ ጊዜ እያካሄደ በሚገኘው  ሲምፖዚየም 26 የፈጠራ ስራዎች ቀርበው በተማሪዎች፣ መምህራንና በአከባቢው ነዋሪ እየተጎበኙ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም