ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ

94

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 07/2014(ኢዜአ)ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በሳይንስ፣ኢኖቬሽን፣ ቴክኖሎጂና ባህል መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ በናይጄሪያ ባደረጉት ጉብኝት ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሃመዱ ቡሃሪ ጋር የሁለቱ አገራት የሁለትዮሸ ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ መምከራቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም ሁለቱ አገራት በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ  ለማድረስ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ሦስተኛው የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ተጠናቋል።

በመድረኩ ሁለቱ አገራት ኢንቨስትመንትና ንግድን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር የተደረገ ሲሆን፤ በዚህም አገራቱ በሳይንስ፣ ኢኖቬሽን፣ቴክኖሎጂና ባህል መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል እና የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዑመር ሳሊሱ ተፈራርመዋል፡፡

በቀጣይም ሁለቱ አገራት በሌሎች መስኮች በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ከዚህ ቀደም የተፈረሙትን ጨምሮ ሁሉም ስምምነቶች በፍጥነት ወደ ትግበራ እንዲገቡ በጋራ ኮሚቴው በኩል ክትትል እንደሚደረግም ተገልጿል።

ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በተለያዩ ዘርፎች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2006 የመጀመሪያውን የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ  በአዲስ አበባ ማካሄዳቸው ይታወሳል።    

ሁለተኛው ጉባኤ በ2017 በናይጄሪያ አቡጃ የተካሄደ ሲሆን፤ ሦስተኛው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ ቆይቶ ዘንድሮ በአዲስ አበባ መካሄድ ችሏል።

ሁለቱ አገራት የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የቀጣይ ስብሰባ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 በናይጄሪያ አቡጃ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም