በባህር ዳርና ደሴ ከተማ ስልጠና ላይ የቆዩ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የመሰረተ ልማቶችን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳርና ደሴ ከተማ ስልጠና ላይ የቆዩ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የመሰረተ ልማቶችን ጎበኙ

ባህር ዳርና ደሴ ሰኔ 7/2014 (ኢዜአ) በባህር ዳርና ደሴ ከተማ ስልጠና ላይ የቆዩ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የመሰረተ ልማቶችን ጎበኙ።
በባህር ዳር ከተማ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ዘመናዊ ድልድይን የፕሮጀክት ምክትል ተጠሪ ማህንዲስ ኢንጅነር ፍቅረስላሴ ወርቁ እንዳሉት ግንባታውን በመጭው ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

ድልድዩ 380 ሜትር ርዝመትና 43 ሜትር ስፋት እንዳለው ጠቅሰው፤ በአንድ ጊዜ 6 መኪኖችን ማስተላለፍ የሚችል ዘመናዊ ድልድይ መሆኑን ገልፀዋል።
"ፕሮጀክቱ 65 በመቶ መጠናቀቁን አመልክተው፤ ግንባታው በመጪው ዓመት መጋቢት ወር 2015 ዓ/ም ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል።
አመራሩ ከድልድይ ፕሮጀክቱ ጨማሮ ሌሎች የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታዎች እየጎበኙ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ በደሴ ከተማ ስልጠና እየወሰዱ ያሉ አመራሮች በ500 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ በከፊል ስራ የጀመረው የኮምቦልቻ እርሻ መሳሪያዎችና ማሽነሪዎች ማምረቻ ፋብሪካ ጎብኝተዋል።
ፋብሪካው የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ ግብርናው ለማዘመን አይነተኛ ሚና እንዳለው የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ገልፀዋል።
የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎችን፣ ትራክተር፣ ሰብል መውቂያና ማጨጃ፣ መኖ ማቀነባበሪያና ሌሎች ማሽኖችን በማምረት የውጭ ምንዛሪውን ከመቀነስ ባለፈ ግብርናውን ለማዘመን አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
ከቻይናና ሌሎች የውጭ ሀገራት አቻ ፋብሪካዎች ጋር በማስተሳሰር በጥራትና በብዛት እንዲያመርትም ክልሉ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በፋብሪካው የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት፣ የብድርና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮችን ለመቅረፍ የክልሉ አመራር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የጀመረውን በከፊል የማምረት ስራ እንዲያጠናክር 400 የእርሻ ትራክተሮችን እንዲገጣጥም ከክልሉ ጋር ውለታ መፈራረሙን ገልጸዋል።
በሽብር ቡድኑ ጉዳት ቢደርስም መልሶ ተቋቁሞ የመኖ ማቀነባበሪያና ሌሎች ማሽኖችን ዳግም ማምረት ጀምሯል፣ ከ300 ለሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎችም የስራና እድል መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።
አመራሮቹ የኮምቦልቻን ችፑድ ፋብሪካና ኢንዱስትሪ ፓርኩን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ላይ የአማራ ክልል በብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።