የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ ጳጉሜን 5/2010 መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክተው የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ። በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች የተሻለ ዓመት እንዲሆን የተመኙት አምባሳደሮቹ አገራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የትብብር ግንኙነት በአዲሱ ዓመትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል። ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ምኞት ያስተላለፉት የቱርክ፣ የህንድ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የስዊዲን፣ አውስትራሊያ፣ የፊላንድና የኮሪያ አምባሳደሮች ናቸው። በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ዩሉሶይ እንደተናገሩት፤ በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአገራቸውም ሆነ በቀጠናው የሰላምና ብልጽግና ስኬትን ተመኝተዋል። ኢትዮጵያውያን ከተለያየ ማንነት የመጡ ህዝቦች ስብስብ ብትሆንም የሚጋሩት አንድ አገርን በመሆኑ ዜጎች ለሚጠቅማቸው አንድነት ትኩረት እንዲሰጡ አምባሳደሩ መክረዋል። "ኢትዮጵያዊያን በአንድ ሠንደቅ ዓላማ ሥር ያሉ መሆናቸውም ኢትዮጵያዊ ያደርጋቸዋል፤ ይህም አንድነቱን ይበልጥ ጠንካራ ያደርገዋል" ብለዋል። በአዲሱ ዓመት ኢትዮጵያ የበለጸገች፣ የተረጋጋችና ጠንካራ አገር እንድትሆንም አምባሳደር ፋቲህ ዩሉሶይ ተመኝተዋል። በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኑራግ ስሪቫስታቫ በበኩላቸው የዘንድሮው የኢትዮጵያዊያን አዲስ ዓመት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከተጀመረው ለውጥ ጋር ተያይዞ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። "ስለዚህም አዲሱ ዓመት 'ኢትዮጵያ' በብዙ መልኩ አዲስ ትሆናለች፤ ምክንያቱም አዲስ የሰላምና የእርቅ ምዕራፍ ተከፍቷል" ሲሉም የህንዱ አምባሳደር ተናግረዋል። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ በዓል የሚከበረው፤ በአገሪቱ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተግባራዊ ሆኖ መሰረታዊ የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ እየተተገበረ ባለበትና ዜጎች በአገሪቱ ላይ ተስፋ እንዲኖራቸው በማድረግ ጭምር መሆኑን ገልፀዋል። በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ሞርጋንም በተመሳሳይ ለኢትዮጵያዊያን አዲሱ ዓመት የሰላምና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል። "ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንዲሁም ለምስራቅ አፍሪካ አገራትም ጭምር አዲሱ ዓመት የሰላምና የብልጽግና ይሁንልን" ሲሉም አምባሳደር ሞርጋን ተመኝተዋል። ለቀጠናው አገራት መሪዎች በተለይም በአገራቸውና በአከባቢው ተስፋ ሰጪ የሰላም ሁኔታ እንዲመጣ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመስግነዋል። በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ቶርብዮን ፒተርሰን የአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸውን ገልጸው፤ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በዚሁ አዲስ ዓመት በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ ምክትል አምባሳደር ሲድ ቻክራብሪቲ ደግሞ ከአዲሱ ዓመት ብዙ ነገር ይጠበቃል ይላሉ። የፊንላንድ ምክትል አምባሳደር ጁካ ፓጃሪኔንም በአገር ውስጥም ከአገር ውጭ ላሉ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ለኢትዮጵያ መንግሥት መልካሙን ተመኝተዋል። "ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲሱ ዓመት ታጠናክራለች፤ በተለይም ግንኙነቱ በንግድ ትብብር ላይ የተጠናከረ እንዲሆን የአገሬ መንግስት ይሻል" ብለዋል። የኮሪያ አምባሳደር ሊም ሆን ሚን አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ብልጽግና ይዞ እንዲመጣ መልካም ምኞት አለኝ ብለዋል። አገሪቱ ልማትን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት አምባሳደሩ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።