ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ሰላምን ለማስፈን መንግስት ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

37

ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ሰላምን ለማስፈን ለሚከናወኑ ተግባራት መንግስት ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራርያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመላ ሀገሪቱ ሰላምን ለማስፈን እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት በሰጡት ማብራርያ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ፍላጎት አንድም ጥይት እንዳይተኮስ ነው ሲሉ አስታውቀዋል።

የህዝቡን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ሰላምን ለማስጠበቅ መንግስት እየሰራ ነው ብለዋል።

በትግራይ ክልልም ብሔራዊ ጥቅምን ባስጠበቀ መልኩ ሰላምን ለማስፈን ለሚከናወኑ ተግባራት መንግስት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ሰብሳቢነት የሚመራ ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል።

‹አማራ ሳያውቅ ድርድር የሚለው አባባል ትክክል አይደለም (TPLF) የኢትዮጵያ ጠላት ነው የተዋጋውም ከኢትዮጵያ ጋር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ናይጄሪያ ተገናኙ ሶርያ ተገናኙ፣ ሶማልያ ተገናኙ የሚለው ተረት ነው፣ ናይጄርያ በነበረን ቆይታ ለአንዲት ሰከንድ ስለሰሜን ጉዳይ አልተነሳም” ብለዋል፡፡

“ውግያ አልደበቅንም፤ ሰላም ለማምጣት መደበቅ አያስፈልገንም፤ የኮሚቴውን ስራ ስንጨርስ ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን” ሲሉ አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል ሰላም ከሰፈነ ቀዳሚ ተጠቃሚ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ መሆኑን አንስተው ለዘላቂ ሰላም ሁሉም ሊረባረብ ይገባል መንግስትም በዚህ ረገድ ሰላምን ለማስፈን ዝግጁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም