በአማራ ክልል 192 ሺህ ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን ዝግጅት ተደርጓል-- የክልሉ ግብርና ቢሮ

62

ባህር ዳር፤ ሰኔ 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር 192 ሺህ ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ተወካይ ዳይሬክተር አቶ እስመላለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም ለአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ለዚህም በመንግስት፣ በግለሰብ፣ በተቋማት፣ በማህበራትና በወጣቶች የተፈላ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላው ከ3 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሳተፉ ጠቅሰው እስካሁን ከ270 ሚሊዮን በላይ የችግኝ ጉድጓድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአንድ ጀምበር ከ250 ሚሊዮን በላይ ችግኝ እንደሚተከልም ተወካዩ ተናግረዋል።  

መርሃ ግብሩ በተያዘለት ጊዜ እንዲከናወን ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ክትትልና ድጋፍ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

"የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ የክልሉን የደን ሽፋን አሁን ካለበት 15 ነጥብ 3 በመቶ ወደ 15 ነጥብ 8 በመቶ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል።

በማህበራት የተደራጁ ከ11 ሺህ በላይ ወጣቶች የደን፣ የፍራፍሬና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በማፍላት በሽያጭ ለተከላ ማዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርና ጽህፈት ቤት የደን ልማት ባለሙያ አቶ መልካሙ ጌቴ በበኩላቸው  ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል።

የተዘጋጁት ችግኞች  ለከተማው ገጽታና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከለው 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኝ 75 በመቶ የሚሆነው ፀድቆ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም