የአጎዋ መዘጋትን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎች እያሉ የወጪ ምርት መጠን አድጓል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

61

ሰኔ 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) “የአጎዋ መዘጋትን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎች እያሉ የወጪ ምርት መጠን አድጓል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመዋል።

“ከሪፎርም በፊት ኢትዮጵያ ሶስት ኢንዱስትሪያል ፓርክ ነበራት፤ ሐዋሳ፣ ኮምቦልቻና መቀሌ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሪፎርም በኋላ ሶስት የአግሮና ዘጠኝ የኢንዱስትሪያል በአጠቃላይ 12 ፓርክ መገንባቷን ተናግረዋል።

በትጋት የሚሰሩ ሰዎች የመኖራቸውን ያህል የሚሰርቅ፣ የሚያላግጥና ወሬ በመተንተን ውጤት የማያመጣ ሰው በመኖሩ መሄድ የሚቻለውን ያህል መጓዝ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል።

ኢንዱስትሪው ያሉበትን የኢነርጂ፣ የሎጂስቲክ፣ የፋይናንስና የቢሮክራሲ ችግር ቢፈታና ኢንዱስትሪው ከ50 በመቶ በላይ ማደግ ቢችል በኢንዱስትሪ ምርት በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ያመጣ እንደነበር ጠቁመዋል።

የአጎዋ አማራጭ ተዘግቶበትና ሌሎች ጫናዎች እያሉበት የኢንዱስትሪው የወጪ ምርት ማደጉን ተናግረዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የገቢ ምርት መተካት ላይ በስፋት በመሰራቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም