በክልሉ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የመዳኘት መብታቸውን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ-ዶክተር ይልቃል ከፋለ

315

ሰኔ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ)“በአማራ ክልል ትክክለኛ ፍትሕ በመስጠት በኩል የሚታዩትን በርካታ ውስንነቶች በመቅረፍ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የመዳኘት መብታቸው ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ” ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

በክልሉ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በዓመት እስከ 750 ሺህ የሕግ ጉዳዮች በመታየት ላይ ናቸው ተብሏል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆችን በተመለከተ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሄዷል።

በክልሉ የፍትሕ ተቋማት ተደራሽነትና እውነትን ፈልፍሎ በማውጣት ትክክለኛ ፍትህ በመስጠት በኩል በርካታ ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በፍትሕ ዘርፉ የሚስተዋሉና ሕብረተሰቡን ያማረሩ ችግሮችን ለመፍታትም የተቀናጀ፣የተደራጀና የተናበበ ስራ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል።

“ፍትሕ ሳይረጋግጥ የዴሞክራሲ ስርአት መገንባት አይቻልም፤የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የመዳኘት መብታቸው ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

ለፍትሕ ስርዓቱ መረጋገጥ ብቃት ያላቸው፣ታማኝ፣ለሕሊናቸው ያደሩና ከራሳቸው ይልቅ የሕዝብ ጥቅም የሚያስቀድሙ ዳኞች ያስፈልጋሉ ነው ያሉት ዶክተር ይልቃል።

የተሟላ የዳኝነት ስርአት ከገነባን ሕዝባችን ያለበትን የፍትህ ስርአት ችግር መፍታት እንችላለን።

በዚህ ረገድም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን በበኩላቸው ''መሰረታዊ ነጻነቶች እውን ይሆኑ ዘንድ ነጻነቱ የተጠበቀና ገለልተኛ የሆነ ተጠያቂነት የሰፈነበት ፍርድ ቤት መኖሩ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው'' ብለዋል።

በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች በዓመት እስከ 750 ሺህ የሕግ ጉዳዮች በመታየት ናቸው።

እያደገ የመጣውን የፍትሕ አገልግሎት ጥያቄ ማስተናገድ የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ ማስፈለጉን ተናግረዋል።

የፍርድ ቤቶችና የዳኞች አስተዳደር ማቋቋሚያ አዋጆች ላይ ማሻሻያ መደረጉንና በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በማወያየት ግብአት የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የተሻሻሉት የሕግ ማዕቀፎች አሁን ካለው ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት(ዩኤስኤይድ) ኢትዮጵያ የፍትሕ ጉዳዮች ኃላፊ ዴቪድ ዲ ጋይልስ ድርጅቱ ለረቂቅ አዋጆቹ ማሻሻያ የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

በውይይቱ ላይ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ኃላፊዎች፣ዳኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም