የኢትዮጵያ እና የናይጄሪያን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የሚያጠናክሩ የተለያዩ አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ተጠቆመ

53

ሰኔ 6/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ እና የናይጄሪያን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር የሚያጠናክሩ የተለያዩ አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸው ተጠቆመ።

አገራቱ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ስምምነቶች በነገው እለት እንደሚፈራረሙም ይጠበቃል።


ሦስተኛው የኢትዮጵያና ናይጄሪያ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ከሁለቱ አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮችና ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

አገራቱ በተለያዩ ዘርፎች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2006 የመጀመሪያውን ስብሰባ በአዲስ አበባ ማካሄዳቸው ይታወሳል።    

ሁለተኛው ጉባኤ በ2017 በናይጄሪያ አቡጃ ሲካሄድ፤ ሦስተኛው በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ ቆይቷል።      

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በናይጄሪያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ሦስተኛው ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።   

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ፍሰሃ ሻውል፤ አገራቱ ለረዥም ጊዜ የቆየ ትብብር ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሁለቱ አገራት ሕዝቦች ይበልጥ ተጠቃሚነት ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ጉባኤው ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረጉ ስምምነቶች መሬት እንዲወርዱ የሚያስችሉ ተግባራት ይከናወናሉም ነው ያሉት።  

የአገራቱ በትብብር መሥራት ለአህጉሩ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ፍሰሃ፤ በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ሊያሰፉ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አብራርተዋል።      

በተለይም ሽብርተኝነትን በመዋጋት የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባም የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንዲሁም በኢንቨስትመንት መስክ ስምምነት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።        

በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በቱሪዝም መስክ በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን እንደሚያደርጉም አመላክተዋል።   

የናይጄሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዑመር ሳሊሱ፤ የኮሮና፣ የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት እንዲሁም ሌሎች ምክንያቶች ለአህጉሩ ፈተና መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም እነዚህን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በትብብር መሥራታቸው ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።     

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የምዕራብ አፍሪካ ዳይሬክተር ኤሊያስ መላኩ፤ ሁለቱ አገራት ከ20 በላይ ስምምነቶችን ቢፈራረሙም ተግባራዊ ማድረግ ላይ ክፍተት መኖሩን ገምግመናል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.ኤ.አ. በ1960 መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም