በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ የፈጠራ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ተሸለሙ

49

አዲስ አበባ ሰኔ 6/2014/ኢዜአ/ በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ፈጠራዎችን በመስራት ተወዳድረው ያሸነፉ ወጣቶች ተሸለሙ።

በሃይፈር ኢንተርናሽናል  ኢትዮጵያ አዘጋጅነት በግብርናው ዘርፍ የፈጠራ ሥራዎች ላይ ያተኮረ የወጣት ፈጠራ ባለቤቶች ውድድር ተካሂዷል።

በፈጠራ ሥራ ውድድሩ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 29 ዓመት የሆኑ እና በኢትዮጵያ ግብርናን ለማሻሻል የሚረዳ የፈጠራ ሃሳብ ያቀረቡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

በውድድሩ 535 ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው ለመጨረሻ ዙር ያለፉት አምስት የፈጠራ ባለቤቶች ተለይተው በዛሬው እለት ተሸላሚዎች ሆነዋል።

የዶሮ እርባታ ዘመናዊ ቤት በመፍጠሯ ወጣት መስከረም የማነ አንደኛ በመውጣት የ10 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆናለች፡፡

በውድድሩ የግራፊክስ እና በይነ-መረብ የግብርና መረጃ በመፍጠር ወጣት ይስሃቅ አምደሥላሴ ሁለተኛ በመውጣት 6 ሺህ 500 ዶላር ተሸልሟል።

በፈጠራ ውድድሩ ሳሙኤል ጌታቸው እና ዮሴፍ ላቀው በጥምረት ለቅድመ-ምርት እና የምርት አሰባሰብ ሳይንሳዊ ዲጂታል የመረጃ ቴክኖሎጂ በመፍጠር በጋራ የ3 ሺህ 500 ዶላር ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን፤ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በተለይም የወጣቶች የፈጠራ ውጤቶች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ከፍተኛ የሰው ቁጥር የሚሳተፍበት በመሆኑ በማዘመን ምርታማነቱን ማሳደግ ለአገር እድገት ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚሁ ዘርፍ እድገት መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም