በኢትዮጵያ የሕትመት ጥራትና የዕውቀት ማዕከላትን ለማስፋት ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ ነው

106

ሰኔ 6/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የሕትመት ጥራትና የዕውቀት ማዕከላትን ለማስፋት ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑን የድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስፈጻሚ ኤልያስ ወንድሙ ተናገረ።

በአሜሪካ የተቋቋመውና በሕትመት ጥራቱና ግዝፈቱ  ከዓለም ስመ-ጥር አሳታሚ ድርጅቶች መካከል አንዱ ነው ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት።

ከአራት ዓመታት በፊት ደግሞ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በሕትመት ጥራትና የዕውቀት ማዕከላትን ለማስፋት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየሰራ ይገኛል።

ምዕራብ ተኮር ይዘቶች ላይ ብቻ የሚያተኩረውን የሕትመት ሥርዓት ሰብሮ የብርሐን ሕትመት የተነፈጋቸውን የኢትዮጵያ ታሪካዊ መጻሕፍት፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ዘመኑን እንዲቀላቀሉ አድርጓል።

በዚህ ዙሪያ በኢትዮጵያ አጠቃላይ የድርጅቱን የሥራ ክንውን በተመለከተ የድርጅቱ ባለቤት እና ሥራ አስፈጻሚ ኤልያስ ወንድሙ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አሳታሚ ድርጅቱ ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን መልከ-ብዙ ፈተናዎች ከውስጥም ከውጭም ቢፈታተኑትም ለትውልድ የሚበጅ ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጿል።

በኢትዮጵያ መነገር ያለባቸው ታሪኮች ተዳፍነው እንዳይቀሩ በመሻት እየሰራ መሆኑን ጠቅሶ፤ በርካታ ታሪኮች ከእውቅ ባለቤቶች እንዲነገሩ አድርጓል ብሏል።

የተሰናሰለ ትርክት ያለው ሰላማዊ እና አንድነቱ የተጠበቀ ጠንካራ የሕዝብ አንድነት እንዲዳብር እውነታዎችን የመሰነድ ሥራዎችን እየሰራ ቢሆንም በተለያዩ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ያሉ አካላት ይህን እንደማይረዱ ኤልያስ ይናገራል።

የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ የዕውቀት ማዕከልነት ተልዕኮውን ለማስፋት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ስመለሆኑም አስረድቷል።

በመጽሐፍት ሕትመት ረገድ በይዘትም ሆነ በሕትመት ጥራት፣ የሕትመት ግብዓት የሚሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና ተያያዥ ችግሮች ለዘርፉ ፈተና በመሆኑ ጠንካራ አሳታሚ ድርጅት እንደሌለ ይገለጻል።

የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት በኢትዮጵያ ለማሳካት የያዛቸውን አውዶች ለማሳካት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ስምምነት እየተፈራረመ መሆኑንም አንስቷል።

ድርጅቱ ከተቋማት ግንባታ መጠናከር ባለፈ ከታዋቂ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚታተሙ የፕሬስ ውጤቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበትን እድል ለማመቻቸት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ለቤተ-መጽሐፍት ግብዓት የማሟላት ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሶ፤ ድርጅቱ የውጭ መጽሐፍት እንዲገቡ የራሱን መርሃ-ግብር ቀርጾ እየሰራ መሆኑን አቶ ኤልያስ ተናግሯል።

ኢትዮጵያ በሃይማኖት አስተምህሮም ሆነ በሳይንሱ ግኝት ምድረ-ቀደምት በመሆኗ ምዕራብ ተኮር የሆነውን ሥርዓተ-ትምህርት በአገር በቀል ዕውቀቶችና ታሪኮች መተካት እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

ኢትዮጵያን በፍቅርና በመተሳሰብ በአብሮነት መዝለቅ እንጂ እርስበርስ አባልተው ሊበታትኑን ለሚሹ የውጭ ኃይላት መጠቀሚያ መሆን አይገባም ብሏል።

በመሆኑም ከትናንት በመማር የፖለቲካ ሥርዓቱን ማሻሻል፣ የተቋማት ግንባታን ማጎልበትና ሥርዓተ- ትምህርትን ትውልድን በሚያንጽ መልኩ ገቢራዊ ማድረግ ያሻል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም