ክልሉ በክረምቱ ወቅት ከ847 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ ለማምረት እየሰራ ነው

53

ሰኔ 6 ቀን 2014 (ኢዜአ) በክልሉ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመቀነስ በተያዘው የክረምት ወቅት ከ847 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት ከ20 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየሰራ መሆኑን የሶማሌ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የግብርና የእንስሳት ሀብት ልማትን በማሳደግ እየተከሰተ ያለውን የድርቅ አደጋን በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

በክልሉ ያለውን የውሃ ሃብት አሟጦ በመጠቀም የፍራፍሬ እና የጓሮ አትክልት ልማት ተደራሽነትን ለማስፋት ሰፊ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በተያዘው የክረምት ወቅትም ከፍተኛ የሰብል ምርት ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል።

በክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተሩ አቶ ባዳል ኪነዲን መሀመድ፤ ክልሉን በተደጋጋሚ እያጠቃ የሚገኘውን የድርቅ አደጋ ለመቀነስ የተደራጀ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

ለዚህም በክረምቱ ወቅት ከ847 ሺህ በላይ ሄክታር መሬትን በማልማት ክልሉን በተደጋጋሚ እያጠቃ ለሚገኝው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከተዘጋጀው መሬትም 20 ሚሊየን 853 ሺህ 874 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዕቅዱ በክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ እና ሌሎች የግብርና ባለድርሻዎች ትብብር የተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወነ ካለው ስራ ጎን ለጎን በ4 ሺህ 350 ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ ለማልማት እንደታሰበ አንስተዋል።

የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን 50 በመቶ ከፍ ለማድረግም ዘመናዊ የማዳቀል፣የክትባት እና የግጦሽ መኖ ተግባራትን በማከናወን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከ21 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የቁም እንስሳት ክትባት በመስጠት ከጎረቤት ሀገራት ሊመጣ የሚችልን የእንስሳት በሽታ ለመከላከል እንደሚሰራም አመላክተዋል።

ዕቅዱን ለማሳካትም ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ቴክኒካል ኮሚቴ በማቋቋም የህብረተሰብ ግንዛቤ በማሳደግ ባለፉት ሁለት ዓመታት በድርቅ ሳቢያ እየተፈተነ ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እንደሚደረግም ተገልጿል።

የክረምቱን ወቅት በሚገባ ለመጠቀም እንዲሁም የመስኖ ልማትን ለማሳደግ ከማህበረሰቡ ጋር በመግባባት ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑም ተነግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም