ሀገራዊ ለውጡን በአዲሱ ዓመትም ለማጠናከር እንደሚደግፉ በጎባ ከተማ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ለውጡን በአዲሱ ዓመትም ለማጠናከር እንደሚደግፉ በጎባ ከተማ ወጣቶች ገለጹ
ጎባ ጶግሜ 5/2010 በአዲሱ ዓመት የአካባቢያቸውን ሰላም በማስከበር ሀገራዊ ለውጡን ለማጠናከር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የጎባ ከተማ ና አካባቢዋ ወጣቶች ገለጹ፡፡ ወጣቶቹ በከገሪቱ በተጀመረው የመደመር፣ የፍቅርና የአንድነት እሳቤ ከዳር ለማድረስ የበኩላችንን ሚና እንወጣለን " በሚል መሪ ሃሳብ በጎባ የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች ካከል ደሱ አብዲሳ እንደተናገረው ቄሮው በየደረጃው ተንሰራፍቶ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊ አሰራሮች እንዲስተካከሉ ባደረገው ተጋድሎና በተመዘገቡ ለውጦች ግንባር ቀደም ሚናውን ተወጥቷል፡፡ "ቄሮው ከታገለለት ዓላማ ውጪ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መልኩ በየቦታው ይደረጉ የነበሩ ተግባራትን ወጣቱ ኃይል በአዲሱ ዓመት በፅናት በመታገል የለውጥ እንቅስቃሴን መደገፍ አለበት "ብሏል፡፡ በሀገሪቱ አሁን በተገኘው የለውጥ እንቅንቃሴ ውስጥ ስራ ፈጥሮ በኢኮኖሚ እራሱን ለመቻል በሚያደርገው እንቅስቀሴ በመሳተፍ የድርሻውን እንደሚወጣ የተናገረው ደግሞ ወጣት ሳዳት አብዱረህማን ነው፡፡ "የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እኔን ጨምሮ በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ራሳቸውን ለመለወጥ ለሚፈልጉ ወጣቶች ሁሉ መነሳሳትን እንፈጥራለን" ብሏል፡፡ ወጣት ሙስና አብደላ በበኩሏ" ሰላም ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደለው በቅርቡ በከተማችን በኃይማኖት ሽፋን ህዝቡን ለማጋጨት ጥረት በተደረገበት ወቅት ከነበረው ሁኔታ ተገንዝበናል" ብላለች፡፡ ወጣቱ ኃይል መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጸሙና ቀጣይነት ያለው ፍትሃዊ ልማት እንዲረጋገጥ የተረጋጋ ሰላሙን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ጠቁማለች፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች በማህበረሰቡ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሳይዘገዩ መፍትሄ ቢሰጣቸው ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን አመኔታ እንደሚጨምር ሌለው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ከዲር ኡስማን ገልጿል፡፡ ወጣቶቹ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ስጋት ተወግዶ ሰላም የሰፈነበት ወቅት በመሆኑ አዲሱን ዓመት በብሩህ ተስፋ ለማክበር ተዘጋጅተዋል፡፡ አዲሱን ዓመት ሲቀበሉም አሁን የተገኘውን ሰላም በማስከበር በሀገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ አጠናክረው የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ህገመንግስታዊ መብቶች እንዲረጋገጡ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ የጎባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ዘይነባ ጣሃ በበኩላቸው ወጣቱ ኃይል በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ በአግባቡ ከተደራጀ ከራሱ አልፎ በሀገር ደረጃ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከንቲባዋ እንዳሉት ወጣቶቹ የሚያነሱትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በተያዘው አዲስ የበጀት ዓመት በትኩረት ይሰራል፡፡