ተጎጂዎች ተገቢውን የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የፈንድ ክፍያን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

73

አዳማ ሰኔ 05/2014 (ኢዜአ) የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች ተገቢውን የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የፈንድ ክፍያን ለማሳደግና አሰራን ለማዘመን እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት አስታወቀ።

ክፍያው የትራፊክ ተጎጂዎች በድንገተኛ ህክምናዎች የሲቲ እስካን፣ ኤም.አር.አይ እና ኤክስሬይ አገልግሎቶችን ጭምር እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑም ተመላክቷል።

አገልግሎቱ ከሁሉም ክልሎችና ከሁለት የከተማ መስተዳድሮች ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በጉዳዩ ላይ በአዳማ ከተማ መክሯል።

የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት የመድህን ኦፕሬሽን ዳይሬቴክተር አቶ አዲል አብዱላሂ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የተሽከሪካሪ አደጋ ተጋጂዎች በመንግስትና በግል የጤና ተቋማት እስከ 2ሺህ ብር የሚያወጣ የድንገተኛ ጊዜ ሕክምና እያገኙ ነው።

ነገር ግን እንደጉዳታቸው መጠን በተሻለ ሕክምና ህይወታቸውን ለመታደግ አሁን እየተሰጠ ያለው አገልግሎትና ፈንድ የሚደረገው 2ሺህ ብር በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል።

"በእዚህም ተጎጂዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እያገኙ አይደለም" ያሉት ዳይሬክተሩ፣ አሰራሩን ለማዘመንና የፋይናንስ ወጪውን ለማሳደግ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተያዘው በጀት ዓመት ከ22ሺህ በላይ የተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች በመንግስትና በግል የጤና ተቋማት የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል።

ለዚህም ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ፈንድ ወጭ ሆኖ ተከፍሏል ነው ያሉት።

የመድረኩ ዓላማም ፈንዱን ለማሻሻል የተካሄደውን ጥናት በግብዓት ለማደበርና ከመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት መሆኑን አስረድተዋል።

የፈንድ መሻሻያ ለማድረግ የሚካሄደው ጥናት ወቅታዊ የሕክምና አገልግሎትን ያገናዘበ እንዲሆን በጥናቱ የጤና ተቋማት፣ የፍትህና ህግ አካላት፣ የትራንስፖርት ሴክተርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መካተታቸውን ተናግረዋል።

"በጥናቱ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች በድንገተኛ ሕክምና የሲቲ እስካን፣ ኤም.አር.አይ እና ኤክስሬይ አገልግሎት ጭምር እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የድንገተኛና ፅኑ ሕክምና ቡድን አባል ሲስተር ምህረት ካሳሁን እንዳሉት፣ ለተሽከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች የሚሰጠው የ2ሺህ ብር የሕክምና አገልግሎት በቂ አለመሆኑን አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ መንገድ ድህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት፣ ከኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ከፍትህ አካላት ጋር በመሆን የፈንድ ክፍያን ለማሻሻል የሚካሄደው ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል።

"የተሽከርካሪ ተጎጂዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እያገኙ አይደለም" ያሉት ሲስተር ምህረት፣ የጤና ተቋማት በቂና ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል የፈንድ ክፍያ ማሻሻያ አስፈላግ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ድንገተኛ የሕክምና አገልግሎት ለሰጡት የጤና ተቋማት ወጪ ያደረጉት ገንዘብ ፈጥኖ እንዲተካላቸው የፋይናንስ የውስጥ ኦዲት አሰራር ጭምር መከለስ እንዳለበት አመልክተዋል።

በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥርና አደጋ ምርመራ ባለሙያ ምክትል ኮማንደር ይሳቅ ቱኬ በበኩላቸው፣ የትራፊክ አደጋ በሀገራችን አስከፊ ገፅታ እንዳለውና ለአካል ጉዳት መከሰት አንዱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

አምራች ሃይሉን እየቀጠፈ ያለውን አደጋ ለማስቆም ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ገልጸው "ክልሎችና የፌዴራል አካላት የአደጋው መንስኤ ተብለው በተለዩት ላይ በጋራ እየሰራን ነው" ብለዋል።

የጤና፣ የትራንስፖርትና በየደረጃው ያለን የፖሊስ ኮሚሽን አባላት ቅንጅታዊ ስራን በማጠናከር የትራፊክ ተጎጂዎች ፈጥነው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የአደጋን መጠን መቀነስ ይጠበቅብናል" ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም