በክልሉ ከመንገድ ጋር በተያያዘ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ ነው-ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ከመንገድ ጋር በተያያዘ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰራ ነው-ቢሮ

አርባ ምንጭ ሰኔ 05/2014 (ኢዜአ) ከመንገድ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከህዝብ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የደቡብ ክልል የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ ።
በጋሞ ዞን ቁጫ አልፓ ወረዳ ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የሞርካ-ቶኮ-ዳንቢያ ጠጠር መንገድ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ እንደገለጹት፣ ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ የተነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አሉ።
እነዚህን የህዝብ ጥያቄዎች ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመፍታት የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ተጀምረው የቆሙ እንዲሁም አዳዲስ መንገዶችን በመገንባት ምላሽ ለመስጠት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ትናንት የተመረቀው የሞርካ-ቶኮ-ዳንቢያ ጠጠር መንገድም ለእዚህ አንድ ማሳያ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
የመንገድ መሰረተ ልማት የግብርና ምርቶችን በቀላሉ ወደገበያ ለማውጣትና የንግድ እንቅስቃሴን በማፋጠን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
"የመንገድ መስፋፋት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የህዝቡን ማህበራዊ ህይወት እንዲጎለብትም ያግዛል" ብለዋል።
የደቡብ ክልል መንገዶች ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘብዴዎስ ኤካ በበኩላቸው፣ የተመረቀው የሞርካ-ቶኮ-ዳንቢያ ጠጠር መንገድ 25 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዳለው ገልጸዋል።
ለመንገዱ ግንባታ ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ጠቁመው፣ መንገዱ ለብዙ ዓመት አገልግሎት መስጠት እንዲችል ህብረተሰቡ በጥንቃቄ እንዲጠቀምበት አሳስበዋል።
በክልሉ መንግስት ድጋፍ የተገነባው ሞርካ-ቶኮ-ዳንቢያ ጠጠር መንገድ መጠናቀቁ የተለያየ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ናቸው።
መንገዱ የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው፣ ለመንገዱ ግንባታ መሳካት የህብረተሰቡ አስተዋጾ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በቁጫ አልፓ ወረዳ ቶኮ ዳንያ ከተማ የሚኖሩት አቶ ምናላቸው ታዲዎስ፣ ከዚህ ቀደም የመንገድ መሰረተ ልማት በአካባቢያቸው ባለመኖሩ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን አስታውሰዋል።
መንገዱ ለአገልግሎት መብቃቱ በምጥ የተያዙ እናቶችንና ህሙማንን በቀላሉ ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም አካባቢው ጤፍ፣ ለውዝ፣ ቅቤ፣ ኮረሪማ እና ሌሎች የግብርና ምርቶች በስፋት የሚመረትበት በመሆኑ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀላሉ ወደገበያ ለማቅረብ መቻሉንና በእዚህም የተሻለ ተጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።