በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን የተሰራው የአፈር ናሙና መመርመሪያ ቴክኖሎጂ ምርታማነት ለማሳደግ ጠቃሚ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን የተሰራው የአፈር ናሙና መመርመሪያ ቴክኖሎጂ ምርታማነት ለማሳደግ ጠቃሚ ነው

ጅማ ሰኔ 5/2014 (ኢዜአ) በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን በትብብር የተሰራው ተንቀሳቃሽ የአፈር ናሙና መመርመሪያ ቴክኖሎጂ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለመጨመር አስተዋጾ እንዳለው ተገለጸ።
ኦሚሽቱ ጆይ' የተሰኘ የአፈር መመርመሪያ ቴክኖሎጂው በአጭር ጊዜ በአፈር ውስጥ ያለውን አሲድ ፣ የንጥረ ነገሮችና የእርጥበት መጠን ውጤት ወደ ሞባይል ስልክ ሪፖርት የሚልክ መሳሪያ መሆኑ ተገልጿል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወጣት ጥጋቡ አብረሐም ለኢዜአ እንደገለጸው በዓለም አቀፍ መድረክ ተሸላሚ የሆነው አፈር መመርመሪያ ቴክኖሎጂው ከ23 ሀገራትና 263 ተወዳዳሪዎች መካከል የተሻለ ሆኖ በመመረጡ ነው፡፡
አነስተኛ መጠን ያለው የአፈር መመርመሪያ መሳሪያው "በአፈር ውስጥ ያሉትን ንጥረ ነገሮችን በመመርመር የትኛው የተክል ወይም የሰብል ዘር ዓይነት ቢለማ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ይለያል" ብሏል።
ለልማት የሚውሉ የአፈር ዓይነቶች የሚያስፈልጋቸው ንጠረ ነገር የትኛው እንደሆነ በመለየት የሚያስፈልገውን የማዳበሪያ መጠን ለማዋቅ ያስችላል ነው ያለው፡፡
'ኦሚሽቱ-ጆይ' በዓለም ባንክ በሚደገፈው 'አፍሪካ እስታርት አፕ' በተሰኘ ድርጅት ተመርጦ አንደኛ በመውጣት የ25 ሺህ ደላር ተሸላሚ ሆኗል፡፡
ወጣት ጥጋቡ ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግ ለመሳሪያው ማምረቻነት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት በስፋት በማምረት ለአርሶ አደሩ በመሸጥ ወይም የአፈር ንጥረ ነገር መመርመሪያ ማዕከላትን በመላው ሀገሪቱ ማቋቋም ያስፈልጋል ብሏል፡፡
የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለመጨመር ጠቀሜታ ያለውን 'ኦሚሽቱ-ጆይ' መሣሪያን በብዛት ለማምረት ጥረት እያደረጉ መሆኑን የገለጸው ወጣቱ መሣሪያውን ለማምረት የሚረዱ ግብዓቶችን ከውጪ ለማስመጣት የምንዛሪ እጥረት ማጋጠሙን ጠቅሷል።
ያጋጠመውን የምንዛሪ እጥረት ችግር ለመፍታትም ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለማሳካት እየሰሩ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ አርሶ አደሮች በድምጽ ትእዛዝ እንዲቀበልና በድምጽ ውጤቱን መግለጽ የሚችል መሆኑን ጠቅሶ የአንዱ መሳሪያ ዋጋ ከ15 እስከ 20ሺህ ብር መሆኑንም ተናግሯል፡፡
"መሳሪያው በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ ፣ በሶማሊኛና በሲዳምኛ፣ ከውጭ ቋንቋ ደግሞ በእንግሊዝኛና በአረብኛ ቋንቋን ትእዛዞችን ተቀብሎ የሚሰራ ቴክኖሎጂ ተግጥሞለታል" ብሏል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአይ ሲቲ መምህር አቶ ጃርሚያ ባይሳ ‘ኦሚሽቱ-ጆይ’ የተሰኘው የአፈር ናሙና መመርመሪያ ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ አፈርን ምርመሮ በአጭር ጊዜ በአፈር ውስጥ ያለውን አሲድ መጠን፣ ንጥረ ነገሮችና የእርጥበት መጠን ሪፖርት ወደ ሞባይል ስልክ የሚልክ መሳሪያ ነው ብለዋል፡፡
መሣሪያው የረቀቀውን ሰው ሠራሽ ልኅቀት ቴክኖሎጂ ከመጠቀሙም በላይ መጠኑ አነስተኛ በመሆኑ ሰዎች በቀላሉ ከቦታ ቦታ ይዘው መንቀሳቀስ የሚችሉት መሰራያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአርሶ አደሩን ያላስፈላጊ የማዳበርያ ወጪ በመቀነስ፣ ለአፈሩ ተስማሚ የዘር ወይም የተክል አይነት በመምረጥ አዋጭና ተስማሚ የሆነውን መርጦ ለማምረት አጋዥ ነው ብለዋል፡፡
መሳሪያውን ለመጠቀም የተለየ እውቀት የሚፈልግ ባለመሆኑ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚጠቅም አስታውቀዋል፡፡
በጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን በትብብር የተሰራ የግብርና ቴክኖሎጂ ነው።