የጎንደርን የሰላምና ልማት ለማጠናከር የክልሉ መንግስት በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው-ዶክተር ይልቃል ከፋለ

111

ሰኔ 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጎንደርና አካባቢውን የሰላምና የልማት ሁኔታ በተጠናከረ ሁኔታ ለማስጠበቅ የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ በጎንደር ከተማ ከሚገኙ የሃይማኖት አባቶች፣የሃገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በከተማዋ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ምክክር እያደረጉ ነው።

በዚህ ወቅት ዶክተር ይልቃል ሰላም የሚረጋገጠው በህዝቡ ቁርጠኛ አቋም በመሆኑ ያለማቋረጥ በመወያየትና መነጋገር ሰላሙን ማረጋገጥ ይግባል ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት የጀመረውን የህግ ማስከበር ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፤ሰላም ለማደፍረስ የሚሯሯጡ የጥፋት ሃይሎችንም ለህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

''በጎንደር ከተማ በቅርቡ የተፈጠረው ግጭት አንገታችን ያስደፋ ነው'' ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ከውስጣችን የበቀሉ አረሞች የፈጠሩት ሴራና ደባ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ጎንደርና አካባቢውን የተረጋጋ የሰላምና የልማት ቀጠና የሚሆንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የሰላም እጦት በክልሉ ከተሞች የኢንቨስትመንት ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ ህዝብ ለሰላሙ መረጋገጥ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ባለው የሰላምና ፀጥታ የምክክር ምድረክ የሃይማኖት አባቶች፣የሃገር ሽማግሌዎች፣ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም