አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል

ሰኔ 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት መፋጠን የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የኢፌድሪ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ፡፡
በጎንደር ከተማ የሚገኘው የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ውጪ ያካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ ዛሬ ለምረቃ በቅቷል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት ሚኒስትሩ እንደተናገሩት አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሀገሪቱ ልማት መፋጠንና ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር በኩል ኢኮኖሚያዊ ድርሻቸውና ተሳትፎአቸው የላቀ ነው፡፡
የዳሽን ቢራ ፋብሪካ በአማራ ክልል መቋቋሙ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር በማህበራዊ ልማትና በስፖርቱ ዘርፍ እያደረገ ያለው ድጋፍና ተሳትፎ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና መጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የከተማና የገጠሩን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጠናከር ረገድ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ፈር ቀዳጅ ኮሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዳሽን ቢራ ግንባር ቀደም መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ናቸው፡፡
ዳሽን ቢራ የክልሉን ልማት በመደገፍ በኩል ባለፉት አመታት ፋና ወጊ የልማት ተግባራት ማከናወኑን የጠቆሙት ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ለፋብሪካው መጠናከር የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግራዋል፡፡
ፋብሪካው የክልሉን አርሶአደሮች የቢራ ገብስ ምርት በመጠቀም የአርሶአደሩ ህይወት እንዲቀየር በማድረግ በኩል ላለፉት አመታት ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡
የፋብሪካው አመታዊ የቢራ ገብስ ግብአት ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ፋብሪካው የሚፈልገውን የግብርና ግብአት በበቂ መጠን አርሶአደሩ አምርቶ እንዲያቀርብ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከውጪ የሚገባውን የቢራ ገብስ በሀገር ውስጥ እንደሚረት በማድረግ በኩል የተሻሻሉ የቢራ ገብስ ዝርያዎችን በምርምር በማፍለቅ ለአርሶአደሩ በማቅረብ በኩል የግብርና ምርምር ተቋማት በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
በ591 ሚሊዮን ብር ወጪ ፋብሪካዊ ያካሄደው የማስፋፊያ ፕሮጀክት አመታዊ የቢራ ማምረት አቅሙን ከ800ሺ ሄክቶ ሊትር ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር የሚያሳድገው ነው፡፡
በፋብሪካው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገርን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የፋብሪካው የፕሮጀክት ማስፋፊያ እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የእውቅና ምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን የፋብሪካው የምርት እንቅስቃሴም በእንግዶች ተጎብኝቷል፡፡