ወጣቱ ትውልድ የሀገር ሉዓላዊነትና አንድነትን የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

79

ጋምቤላ ሰኔ 4/2014 (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ የሀገር ሉዓላዊነትና አንድነትን የማስጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስገነዘቡ።

በህልውና ዘመቻው ግዳጃቸውን በብቃት ፈጽመው ለተመለሱ የክልል ልዩ ኃይል አባላት የማዕረግ እድገትና የእውቅና አሰጣጥ መረሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።   

ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት ቀደምት አባቶች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቀለም ሳይከፋፈሉ በአንድነትና ጀግነት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት አስጠብቀው ቆይተዋል።

የአሁኑ ትውልድ የሀገሩን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት የመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድንና ሌሎች የውጪ ግበረአበሮቹ ሀገሪቱን ለማፍረስ የከፈቱትን ወረራ ለመቀልበስ የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት በግንባር በመሰለፍ ያሳዩት ጀግንነትና ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የልዩ ኃይሉ አባላት የሽብር ቡድኑና ተላላኪዎቹ የጠነሰሱትን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለማክሸፍ ላሳዩት ጀግንነትና ተጋድሎ የክልሉ ህዝብና መንግስት ታላቅ ኩራት  መሆኑን ተናግረዋል።

በዕውቅናና ማዕረግ የተሰጠው በቆይታቸው ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በድል ላጠናቀቁ አባላት መሆኑን ርዕሰ መስተዳሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው በበኩላቸው የልዩ ኃይል አባላቱ በተሰጣቸው የግዳጅ ቀጠና በድል በመወጣት ያሳዩት ጀግንነት ክልሉን ከፍ ያደረገ ነው ብለዋል።

"በቀጣይም የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉ የጥፋት ቡድኖችን በማምከን ዳግም ጀግንነታቸውን ማሳየት አለባቸው ብለዋል።

ከግዳጅ ከተመለሱት የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት መካከል ኮማንደር ቻም ኡቦንግ በሰጡት አስተያየት በተሰጣቸው እውቅና ከፍተኛ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን በመግለጽ በቀጣይም በሀገር ሉዓላዊነት የሚቃጣ ወረራ ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ማንኛውንም የፀጥታ ችግር ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን የገለጸው ደግሞ ሌላው የልዩ ኃይል አባል ምክትል ኮማንደር አብረሃም አቡላ ናቸው።

በህልውና ዘመቻው ግዳጃቸውን በብቃት ፈጽምው ለተመለሱት የልዩ ኃይል አባላት የማዕርግ እድገት፣ የገንዘብና የምስክር ወረቀት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የተበረከተላቸው ሲሆን በግዳጅ ለተሰው አባላት ቤተሰቦችም የ150 ሺህ ብር የገንዝብ ድጋፍ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም