ህብረተሰቡ በፍቅር ተደምሮ አዲሱን ዓመት በይቅርታ እንዲሻገር እንመኛለን-ተኝተው ታካሚ ህሙማን - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡ በፍቅር ተደምሮ አዲሱን ዓመት በይቅርታ እንዲሻገር እንመኛለን-ተኝተው ታካሚ ህሙማን
አዲስ አበባ ጳጉሜ 5/2010 ህብረተሰቡ በፍቅር ተደምሮ አዲሱን ዓመት በይቅርታ እንዲሻገር በሆስፒታል ተኝተው ህክምና በመከታተል ላይ ያሉ ህሙማን ተናገሩ። አዲስ ዓመት ሲመጣ በየአካባቢውና በየሰፈሩ በዓል በዓል የሚያስመስሉ ክስተቶች ትልቅ ድምቀት ይሰጡታል። በተለይም ዓመት በዓልን ከወዳጅ ዘመድ ፣ ቤተሰብ ፣ ጎረቤት፣ ከባልንጀራ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ተሰባስቦ ማሳለፍ ደግሞ ይበልጡኑ ደስታን ያቀዳጃል። ታዲያ በተለያዩ የጤና እክል ምክንያት በዓላትን በሆስፒታል ተኝተው የሚያሳልፉ ወገኖችም መኖራቸው እሙን ነው። ኢዜአ ያነጋገራቸው በሆስፒታል ተኝተው ህክምና የሚከታተሉ ታማሚዎች አዲስ ዓመትን በሆስፒታል ማሳለፍ ያለውን ስሜት እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል። አቶ ተወልደ ገብረእግዚአብሔር “የህክምናው ክትትልና ድጋፋቸው በጣም ጥሩ ነው። በቅርቡ ደግሞ ድኜ እንደምወጣ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ። “ ብለዋል፡፡ በዓልን በሆስፒታል ማሳለፍ ያጋጣሚ ጉዳይ ነው። ሁል ጊዜ ጤነኛ መሆን አያቻልም ትታመማለህ ትድናለክ ስለሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም በዓል እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ “ሰላምና መልካም ግንኙነት ካለ ምንም የሚጠፋ ነገር የለም ተከፋፍለን መኖር መጥፎ ነው ስለዚህ ለመጪው አዲስ አመት አብረን ብንሰራ ብዬ መልዕክቴን አስተላልፋለው። ወጣት ዘይነባ አብርሃም በበኩላ ”ዓመት በዓል ከቤተሰብ ውጭ ማሳለፍ ቢያስጠላም ጤና አግኝቶ መመለስ ደግሞ የግድ ነው በመሆኑም ሁለት ወዶ ስለማይሆን አዚህም ሆኖ በሰላምና በደስታ ማሳለፍ ይችላል፡፡” ስትል ተናግራለች፡፡ የታካሚዎች አስታማሚዎች በበኩላቸው በዓሉን ከቤት ተለይቶ ሀኪም ቤት ማሳለፉ ትንሽ የሚከብድ ቢሆንም ጤናው ቀዳሚ ሰለሆነ ባሉበት ሆነው በደስታ ለማሳለፍ ጥረት አናደርጋለን ብለዋል። አቶ ተስፋዬ ወልደሰንበት የተባሉ አስታማሚ በበኩላቸው "ሰው መኖር ሲችል ነው ዓመት በዓልን ማሰለፍ የሚችለው ያ ካልሆነና ሰው ከሌለ ደስተኛ ሆኖ ለመኖር ስለማይቻልና ህይወትን ለማዳን እዚህ ቁጭ ማለታችን አይከፋንም ብለዋል።