በክልሉ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል

105

ሰኔ 4/2014/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሽመልስ አብዲሳ ይህንን ያሉት በኦሮሚያ ክልል በዱከም ከተማ የተገነባ ታዳሽ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ በተመረቀበት ጊዜ ነው።

ፋብረካው 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን በ50 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አርፏል።  

ፋብሪካው በቀን 600 ቶን ፌሮ ብረት የማምረት አቅም ያለው ሲሆን 700 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል ተብሏል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ፋብሪካው ሥራ መጀመሩ የአገሪቱን የብረት ፍላጎት በአገር ውስጥ ምረት ለመተካት ያስችላል።

አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚያስችላት ገልጸው በተለይም ጥቅም ላይ ያልዋሉ ብረቶችን መልሶ ለመጠቀም ትልቅ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

በመሆኑም ዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለአገራችን ትልቅ ባለውለታ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፤ ሌሎችም ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ መንግሥትም በዘርፉ ለተሰማሩት የግል ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ዘርፉን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።

በሌላ በኩል የክልሉ መንግሥት በክልሉም ሆነ በአገሪቱ ላይ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ባሉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል።

ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ የብረት ጥሬ ዕቃውን በአገር ውስጥ በመጠቀም የሚያመርት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፋብሪካው ባለቤት አቶ ክብሩ ይስፋ ናቸው።

ይህም የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት ረገድ አገራዊው ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት።

ሌሎች ባለሃብቶችም በዘርፉ በመሰማራት ለአገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።

በፋብሪካው የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሰዎች በበኩላቸው በፋብሪካው እየሰሩ በሚያገኙት ገቢ ቤተሳባቸውን እያሰተዳደሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፋብሪካው በሚጠቀመው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የክህሎት ዕውቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በፋብሪካው ምርቃት መርሃ ግብር የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ታከለ ኡማ ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም