ለሀገር ልማትና የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሙስናን በተደራጀ መንገድ መከላከል ያስፈልጋል

107

ሚዛን አማን፣ ሰኔ 04/2014 (ኢዜአ) ለሀገር ልማትና የዜጎችን ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሙስናን በተደራጀ አግባብ መከላከል እንደሚያስፈልግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፍትህ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በሙስና ወንጀል ህግና የሙስና ወንጀል ምርመራ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላትና ዐቃቤ ሕግ ባለሙያዎች ጋር በሚዛን አማን ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ እንደገለጹት ሙስና ሀገርና ህዝብን የሚጎዳ አስከፊ ወንጀል ነው።

ሙስና በሀገር ዕድገትና የዜጎች ተጠቃሚነት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ወንጀሉን የሚፀየፍ ትውልድ መፍጠር ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት ብለዋል።

የሙስና ወንጀል ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሚዛን ከማዛባት ባሻገር የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚያስከትልም ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በፍትህ ስርዓት ውስጥ ሲታይ የነበረው የተንዛዛ የዳኝነት ስርዓት ሙስናን ማስፋፋቱን ኃላፊው አመልክተዋል።

ቀልጣፋና ፈጣን የዳኝነት  ሥርዓትን በመዘርጋት ሙስናን መከላከልና መቆጣጠር ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ገነት መንገሻ በበኩላቸው ፈጣንና ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የፍትህ ሥርዓቱን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የክልሉ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር የህብረተሰቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ሙስናን በመከላከልና ሙሰኞችን በማጋለጥ ዜጎች እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

የፍትህ ተቋማት ክልሉ መልካም አስተዳደር የሰፈነበትና ከሙስና የጸዳ መዋቅር በመዘርጋት፤ በግልጸኝነትና በተጠያቂነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

በሚዛን አማን ከተማ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው በክልል አቀፍ የምክክር መድረክ የዐቃቤሕግ ባለሙያዎች፣ መርማሪዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም