ቤተክርስቲያኗ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ድጋፍ አደረገች

86

ሰኔ 4/2014 ነቀምቴ (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ማዕከላዊ ሲኖዶስ ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ሁለት ወረዳዎች በጸጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች፡፡

የሲኖዶሱ የልማትና ማህበራዊ  አገልግሎት ኮሚሽን ዳይሬክተር አቶ ተሰማ ጃለታ እንዳስታወቁት ድጋፉ የተደረገው ከጉቶ ጊዳ እና ሳሲጋ ወረዳዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ከመኖሪያ ቤታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በትላንትናው እለት ለ1ሺህ 848 ቤተሰቦች ድጋፍ መደረጉን ያስረዱት ዳይሬክተሩ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 462 ኩንታል የፋብሪካ ማዳበሪያና 116 ኩንታል ምርጥ ዘር በቆሎ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣይም የዩሪያ ማዳበሪያና ለእንስሳት ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶችና ሌሎች ቁሶችን ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅሰዋል።

ከሳሲጋ ወረዳ የተፈናቀሉት አርሶ አደር ኢተፋ ታደሰ  በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት መኖሪያ ቤታቸውን ጨምሮ ሀብት ንብረታቸው አጥተዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ቢመለሱም ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ገዝተው  የግብርና ስራቸውን ለመስራት ከአቅማቸው በላይ መሆኑን በማየት ቤተክርስቲያኗ ላደረገችላቸው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የበዳሣ ጃርሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምሥጋኑ ቢቂላ እንዳሉት በግጭቱ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በቤተክርስቲያኗ የተደረገላቸው ድጋፍ ካጋጠማቸው ችግር ለመውጣት መነሻ እንደሚሆናቸው አመልክተው።

ከጉቶ ጊዳ ወረዳ የተፈናቀሉት  አርሶ አደር ቦቦ ወልተጂ በበኩላቸው ያገኙትን የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ድጋፍ በመጠቀም ራሳቸውን ለመቻል መነሻ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል።

ስለተደረገላቸው ድጋፍም መደሰታቸውንና ቤተክርስቲያኗ ከጎናቸው በመቆሟ  ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም