በአዲሱ ዓመት የለውጥ ሂደቶችን ለማጠናከር ይሰራል---ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን ማቴዎስ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት የለውጥ ሂደቶችን ለማጠናከር ይሰራል---ርዕሰ መስተዳድር ሚሊዮን ማቴዎስ
ሀዋሳ ጶግሜ 5/2010 በአዲሱ ዓመት በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ የተጀመሩ የለውጥ ሂደቶችን ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ አስታወቁ ። ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱን ዓመት በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዚሁ መልዕክታቸው ላይ እንዳሉት የተጠናቀቀው ዓመት በክልሉ ግጭቶች የተስተናገዱበት፣ የሰዎች ህይወት የጠፋበት፣ ንብረት የወደመበትና በርካቶች የተፈናቀሉበት ሆኖ አልፏል ። በሌላ በኩል ደግሞ የፀጥታ ስጋቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተፈቱበት፣ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር የተካሄደበትና አዲስ የለውጥ ጉዞ የተጀመረበት እንደነበርም ጠቅሰዋል ። "በአዲሱ ዓመት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱና የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው በትኩረት ይሰራል " ብለዋል ። ለውጡን ለመላው ህዝብ በሚጠቅም መልኩ ለማስኬድ መልካም የሚባሉ የተጀመሩ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶች እንዲቀጥሉ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል ። "መታረምና መስተካከል ያለባቸው፣ ህዝብን ያስኮረፉና ከፍትሀዊነት አንጻር ጥያቄ የተነሳባቸው ጉዳዮችን በማረም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ይሰራል" ብለዋል። የክልሉ መንግስት የዜጎች ሰላምና ደህንነት እንዲከበር፣በየትኛውም የክልሉ አካባቢ ተንቀሳቅሰው ሀብት የማፍራት፣ የመስራትና የመኖር መብታቸውን የማስከበር ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ በህዝቡ ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት እንዳለ የተናገሩት አቶ ሚሊዮን በገጠርና በከተማ ከወጣት እስከ አዛውንቱ ያለውን የለውጥ ፍላጎት እንደሚደግፉም አመላክተዋል ። "የለውጥ ሂደቱን በስጋት የሚያዩ አመራሮችና ባለሙያዎች ያሉ በመሆኑ ልንታገላቸው ይገባል " ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ ። ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱ አመት ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፣የሰላምና የፍቅር እነዲሆን ምኞታቸውን ገልፀዋል።