የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል አሰራር ተፈጻሚ ሊሆን ነው

145

ሰኔ 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል አሰራር ተፈጻሚ ሊሆን ነው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይህንኑ አሰራር በሦስት ወራት ውስጥ ተፈጻሚ ያደርጋል ተብሏል።

የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ የሁሉም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና የትምህርት ሚኒስቴር  ከፍተኛ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ሁሉም ተግባራዊ እንዲያደርጉ ምክክር ይደረጋል።

አሰራሩ ዩኒቨርሲቲዎች አቅማቸውን በማጎልበት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ሲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ይህንኑ አሰራር በሦስት ወራት ውስጥ ተፈጻሚ ያደርጋል ተብሏል።

የዩኒቨርሲቲዎች ራሳቸውን የማስተዳደር አሰራር መንግሥትን ከከፍተኛ ወጪ በማዳን በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ መስክ ጉልህ ሚና የሚኖረው ይሆናል።

በሰው ሀብት አስተዳደር፣ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ፣ የምርምር ማዕከላትን በማጠናከር፣ በፋይናንስና የአካዳሚክ ነጻነትን በማረጋገጥ የላቀ ሚና እንደሚኖረውም ታምኖበታል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነጻ ሆነው ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ በመንግሥት በኩል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም