በአፋር ክልል የአፍዴራ መብራት ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል

ሰመራ ሰኔ 4/2014 (ኢዜአ) በአፋር ክልል ከ1ነጥብ 1ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የአፍዴራ የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሚኒኬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞገስ ሞኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ግንባታው ከፍተኛ የሃይል ተሸካሚ ማማዎች ተከላን ጨምሮ የሰራተኞች መኖሪያ፣ የመጠጥ ውሃ ጉድጎድ ቁፋሮና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን ያካተተ ነው።

ሰመራ ከሚገኘው ማከፋፈያ ጣቢያ በ230 ኪሎ ቮልት መስመር ላይ  ሃይል በመቀበል እስከ 25 ሜጋ ዋት ኃይል የሚሰጥ አንድ ባለ 31.5 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመር ተከላም ሌላኛው የጣቢያው ግንባታ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።


"ጣቢያው በሀገር አቀፍ ደረጃ በጨው ምርቷ ለምትታወቀው አፍዴራ ወረዳ የ24 ሰዓት የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የሃይል ማከፋፈያው በአካበቢው አየተስፋፋ የመጣውን የአይወዳይዝድ ጨው ማቀነባበሪያና ሌሎች የኬሚካል ኢንደስትሪዎችን የሃይል ፍላጎትን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።    

ግንባታው ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 20 ሚሊዮን ዶላር ብድርና የኢትዮጵያ መንግስት በበጀተው 169 ሚሊዮን ብር ጨምሮ በአጠቃላይ ከ1ነጥብ1ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

 
ግንባታው በአካባቢው ያለውን ከፍተኛ ሙቀትና ንፋስ መቋቋም የሚያስችል ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያካተተም መሆኑን ጠቁመዋል።


በተጨማሪም ለማከፋፈያው ተገልጋዮች የሃይል መቆራረጥን ለማስቀረት ለማከፋፈያ ጣቢያው ብቻ የሚያገለግል 392  ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል 60 የፀሐይ ኃይል መሰብሰቢያ ፓኔሎች  እንደተገጠሙለት ተናግረዋል።

የሃይል ማስተላለፊያ መስመሩ "ካልፓቱሮ" የሚባል የህንዱ ኩባንያ እና የጣቢያው ግንባታ የቻይናው "ናንጂንግ ዳጂ" በሚባል ኩባንያ የተገነባ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአፋር ሪጂን ሃላፊ አቶ ያሲን አሊ እንዳሉት ወረዳው ከፍተኛ የኢንቨስተመንት እንቅስቃሴዎች የሚደረግበት ቢሆንም በቀን ለ6 ሰዓት ብቻ በጀኔረተር በመታገዝ የኤሌክትሪክ ሃይል ሲያገኝ ቆይቷል።
 
መንግስት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ማከፋፈያ ጣቢያ ገንብቶ በማጠናቀቅ የአፍዴራና አካባቢዉን ማህበረሰብ የመብራት የሃይል ተጠቃሚነት ጥያቄ የመልስ ነው ብለዋል።

የማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት መጀመር በአካባቢው እያደገ የሚገኘውን ኢንዱስትሪ ፍሰት ከማነቃቃት ባለፈ የአጎራባች የኢረብቲና ቢዱ ወረዳ ነዋሪዎችን የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የወረዳው ነዋሪ  ወይዘሮ ሰኢዳ ኡመር  በሰጡት አስተያየት  ከፍተኛ ሙቀት ለመቋቋም የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም መብራት ባለመኖሩ በተለይም ሴቶችና ህጻናት ሲቸገሩ እንደነበር ገልጸው ችግሩ በመፈታቱ መደሰታቸውን ነው የተናገሩት።


የመብራት ተጠቃሚ መሆን መቻላቸው ከግል ኖሯቸው ባለፈ የጨው ምርትን ለማሳደግ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ለመጠቀም እንደሚያስችላቸው  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም