ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል

82

ሐረሪ፤ ሰኔ 3 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ በተሰራው ሥራ የተመዘገበውን ውጤት ማስቀጠል እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በክልሉ ሰላምን ለማስጠበቅ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ የክልሉ ምክርቤት አፈጉባኤ በተገኙበት ከክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት ጋር ተወያይቷል።

በውይይቱ የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ማህበረሰቡን በማስተባበርና የሰላም አደረጃጀቶችን በመፍጠር ሥራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ዋደራ አብራርተዋል።

የክልሉን የፀጥታ ተቋማት ወቅቱን በሚመጥን ደረጃ ለማደራጀትና ለማጠናከር የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል።

የክልሉ ጠቅላይ አቀቤ ህግ አቶ አዩብ አህመድ በበኩላቸው፣ በክልሉ የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተሰራው ሥራ የህብረተሰቡን ሰላም ለማወክ በተንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮምቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰላምን ለማስጠበቅ የተሰራው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት የተስተዋሉ መፈናቀል፣ ዝርፊያና መሰል ተግባራትን ከማስቆም አንፃር አበረታች ስራ ማከናወኑን የገለፁት ደግሞ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማህዲ ናቸው።

የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንዲያስቀጥለም አሳስበዋል።

የሰላም ጉዳዮች ንኡስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር የሺመብራት መርሻ በበኩላቸው፣ የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተጀመሩ ስራዎች በአርአያነት የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ህዝቡ በሰላሙ ጉዳይ በማሳተፍ የተሰራው ሥራ ለሌሎች ተሞክሮ ስለሚሆን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ ሳዲቅ አደም በበኩላቸው ካሁን ቀደም በምስራቁ የሃገሪቱ ክፍል አጎራባች ክልሎች በሰላም ጉዳይ ላይ ተሳስረው ይሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

"የቀድሞውን ግንኙነት በማጠናከር ሰላምን ዘላቂ ከማድረግ ባለፈ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያስችላል" ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በክልሉ የነበረው መቻቻል ባጋጠሙ ችግሮች መሸራረፍ አጋጥሞታል ያሉት የሃረሪ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም ቀድሞ የነበሩ የመቻቻል እና አብሮነት የሰላም እሴቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ገልፀዋል፡፡

አፈ ጉባኤው በክልሉ ያሉ የአብሮነት እና የመቻቻል እሴቶችን በመሰነድ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋፋት እንደሚሰራም ገልፀዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም