ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያን መገንባት ይጠበቅብናል-ኮሚሽኑ

73

ጋምቤላ ሰኔ 3/2014/ኢዜአ/ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያን በመገንባት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽነር አስታወቁ።

ኮሚሸኑ ከጋምቤላ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር የትውውቅና የምክክር መርሃ ግብር ዛሬ በጋምቤላ ከተማ አካሄዷል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌጡ እንዳሉት ችግሮችን በአካታች ውይይቶች በመፍታት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምንና ልማትን ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት መሳካት የህዝቡ ተሳትፎ ዓይነተኛ ሚና አለው።

ኮሚሽኑ በአገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ልዩነቶችንና ያለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ሰላም የሰፈነባትና ለህዝቦቿ የምትመች ኢትዮጵያን ለመገንባት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሚሽኑ ለተጀመሩት ሰራዎች መሳካት መላው ህዝብ እውነተኛና ምክንያታዊ ሃሳቦችን በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት የክልሉ ህዝብና መንግሥት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ለጀመራቸው ሥራዎች ስኬታማነት ከጎኑ እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር ለተቀየሰው አገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም በባለቤትነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ የአመራርና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ በየአካባቢያቸው ጠንክረው እንዲሰሩ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም