በክልሉ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችን አቅም ለማጠናከር እየተሰራ ነው

ሀዋሳ ሰኔ 03/2014 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልል ሥራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በክልሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆችን አቅም ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ቢሮው በ30 ሚሊዮን ብር የገዛቸውን የተለያዩ ማሽኖች ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ዛሬ አስረክቧል፡፡

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የቢሮ ሃላፊ ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ እንደገለጹት፣ ቢሮው ከ85 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ኮሌጆቹን ለማጠናከር እየሰራ ነው።

ከበጀቱ 55 ሚሊዮኑ በተለያየ ምክንያት የዘገዩ ኮሌጆች ግንባታ ማጠናቀቂያነት የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

ማሽነሪዎቹ የትምህርትና ስልጠናውን ጥራት ለማሻሻል የሚረዱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የቢሮው ምክትልና የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ዴዊሶ ኮሌጆቹ 70 ከመቶ በተግባር የተደገፈ ስልጠና የሚሰጡ በመሆናቸው ለ11 የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች ከ150 የሚበልጡ ማሽነሪዎችን በ30 ሚሊዮን ብር በመግዛት ማስረከባቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ እንዳሉት ማሽኖቹ ለግብርና ማቀነባበሪያ፣ ለኮንስራክሽን፣ ለጨርቃጨርቅና አልባሳትና ለግንባታ ዘርፍ የተግባር ስልጠናዎች የሚውሉ ናቸው።

ሥራውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የሚደግፉ 60 ኮሚፒዩተሮች በድጋፉ መካተታቸውን ገልጸዋል፡፡

ማሽኖቹ በዋና ዋና ስልጠናዎች ላይ ያለውን የተማሪና የማሽነሪ ጥምርታ ለማጣጣም ታስበው የተገዙ መሆናቸውን ገልጸው "ኮሌጆቹ የታለመላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ ድጋፉ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

ዛሬ ማሽኖችን ከተረከቡት ተቋማት መካከል የሃዋሳ ተግባረዕድ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ዲን አቶ መልካሙ ባራሳ በትምርትና ስልጠና ዘርፉ የፖሊሲና ስትራቴጂ ለውጥ በመደረጉ አዳዲስ ፍላጎቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

"በድጋፉ በተለይ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሃይል ለማምረት የሚያስችሉ 13 ማሽኖችንና ስልጠናውን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችሉ ኮምፒዩተሮችን ተረክበናል" ነው ያሉት።

ኮሌጃቸው አዲስ በመሆኑ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይልና የማሽነሪ እጥረት ችግራቸው እንዲፈታ ተደጋጋሚ ጥያቄ ለክልሉ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ደግሞ የቀባዶ ኮንስትራክሽና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ደግፌ አለማየሁ ናቸው፡፡

የተረከቧቸው ማሽነሪዎች ብቁ የሰው ሃይል ከማፍራት ባሻገር የአካባቢውን ችግር መፍታት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማፍለቅ የሚረዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ከሚገኙ 11 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች መካከል ሁለቱ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም