በክልሉ በሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ይከተባሉ

45

ጂንካ ሰኔ 3/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ዘመቻ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ ተገለጸ ።

የክትባት ዘመቻው ዛሬ በጂንካ ከተማ ተጀምሯል።

በደቡብ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶችና ህጻናት ጤናና ስነምግብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ለቺሶ እንዳሉት፣ በክልሉ በ1ኛ እና በ2ኛ ዙር የክትባት ዘመቻ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ተከትበዋል።

ለስምንት ቀናት በሚቆየው ሦስተኛ ዙር የክትባት ዘመቻም 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎችን ለመከተብ ታቅዶ ከትናንት ጀምሮ በሁሉም የክልሉ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ክትባት መጀመሩን ገልጸዋል።

ለክትባቱም ጆንሰንና ጆንሰን ፣ ፋይዘር፣ አስትራዜኒካና ሲኖፋርም የተሰኙ ክትባቶች መሰራጨታቸውን ገልጸዋል።

ሦስተኛውን ዙር የኮቪድ-19 የክትባት ዘመቻ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ ያስጀመሩት የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አታ ናቸው።

ህብረተሰቡ የበሽታውን መከላከያ መንገዶች በአግባቡ አውቆ ከመተግበር ይልቅ መዘናጋት እየተስተዋለበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በክትባቱ ላይ የሚናፈሰው የተዛባ አስተያየት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከል ሥራውን ፈታኝ አድርጎታል።

እስካሁን በኮቪድ-19 ላይ የተደረጉ ጥናቶች ከትባቱን ከወሰዱት ሰዎች ይልቅ ክትባቱን ያልወሰዱት በቫይረሱ ሕይወታቸውን የማጣትና ለከፋ የጤና ችግር የመጋለጥ እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በዞኑ በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር የክትባት ዘመቻ 200ሺህ የማህበረሰብ ክፍሎችን መከተብ እንደተቻለም አቶ አብርሀም ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ በሦስተኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ወደ 230 ሺህ የሚጠጉ እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ለመከተብ እየተሰራ ነው።

ክትባቱን በመውሰድ ያስጀመሩት የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉዲሼ፤ ኮሮናቫይረስ በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የራሱን ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል።

በትምህርት ተቋማት ከየትኛውም አካባቢ በላይ የህዝብ ጥግግት ስለሚኖርና በእዚህም ለቫይረሱ ተጋላጭነት ስለሚጨምር ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ክትባቱን መውስድ እንዳለበት አሳስበዋል።

በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረው የሦስተኛው ዙር የክትባት ዘመቻ ለ8 ተከታታይ ቀናት እንደሚካሄድ ታውቋል።

ለክትባቱ ስኬታማነት የሃይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም