የእምነት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶች የጋራ ሃብት እንጂ የጥላቻና ግጭት ምክንያት ሊሆኑ አይገባም

ሰኔ 3 ቀን 2014 (ኢዜአ በኢትዮጵያ የእምነት፣ የቋንቋና የባህል ልዩነቶች የጋራ ሃብት እንጂ የጥላቻና ግጭት ምክንያት ሊሆኑ አይገባም ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ የተለያዩ እምነት ተከታዮች በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመረዳዳትና በአንድነት የሚኖሩባት፣ የታሪክ፣ የቋንቋና የባህል ውቅያኖስ መሆኗ ይታወቃል።

እነዚህ ሁሉ አይነተ-ብዙ ልዩነቶች ደግሞ ውበት ሆነው ዘመናትን ተሻግረው ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንዶች ልዩነቶችን የግጭት ምክንያት ለማድረግ የኢትዮጵያዊያንን የቆዩ እሴቶች ለመሸርሸር ብዙ ሲጥሩ ይስተዋላል።

እነዚህ እኩይ ዓላማ ያነገቡ ኃይሎች በርካታ የግጭት ቀስቃሽ ሙከራዎችን ቢያደርጉም በአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እየከሸፈ ዓላማቸው እየመከነ ይገኛል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡለማ ምክር ቤት አባል እና የሰላምና እርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሼኽ መሃመድ ሲራጅ፤ በኢትዮጵያ የሃይማኖት፣ የቋንቋም ይሁን የባህል ልዩነቶች ቢኖሩም በአገር ጉዳይ ግን ሊበተን የማይችል አብሮነት መኖሩን ይናገራሉ።

"የተለያዩ እምነቶችና ብዙ ማንነቶች ቢኖሩንም አገራችን አንድ ነች" ያሉት ሼኽ መሃመድ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማትና እድገት መጋራት ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

በርካታ ዓማኞች ባሉባት ታላቅና ጥንታዊት አገር ኢትዮጵያ ልዩነቶችን የጥላቻና የቅራኔ ምክንያት በማድረግ ጦርነትና ግጭት መፍጠር አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም እምነትና ብሔርን የልዩነትና የግጭት ምክንያት ለማድረግ የሚጥሩ መኖራቸውን ጠቁመው፤ ለእነዚህ አካላት በፍጹም ቦታ ልንሰጣቸው አይገባም ብለዋል።

የእምነት ተቋማትም ሰላምን፣ አብሮነትንና መተዛዘንን በሚገባ በመስበክ ኢትዮጵያን በጋራ ለማሳደግ የሚጥር ማኅበረሰብ መፍጠር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

"አብሮነት፣ መተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ማዘን፣ መልካም ስብዕና እና ርህራሄ" የሰው ልጅ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ የእምነት አስተምህሮዎችም ይህንኑ የሚያረጋግጡ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁላችንም ተቀራርበን እንስራ ሲሉ ጠይቀዋል።

ከጥላቻና ግጭት ኪሳራ እንጂ ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅም ትርፍ የማይገኝ በመሆኑ ሰላምና አብሮነትን የዘወትር መርሃችን አድርገን መንቀሳቀስ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዝዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ በበኩላቸው፤ ዓለም መተባበርን እየሰበከ ባለበት ወቅት ለልዩነትና መቃቃር የሚሰሩ ኃይሎችን ልንቀበላቸው አይገባም ነው ያሉት።  

ኢትዮጵያዊያን ከግጭትና ጥላቻ አስተሳሰብ ወጥተን ለአብሮነታችን የምንሰራበት ጊዜ አሁን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ብሔርን፣ ወሰንን፣ ሃይማኖትንና ሌሎች ምክንያቶችን የግጭት መነሻ ከማድረግ በመቆጠብ የጋራ ቤት ለሆነችው አገር ሰላም መስበክ አለብን ብለዋል።

ከቤተሰብ ጀምሮ የእምነት ተቋማት ግብረገብነትን ማስተማር ላይ ትኩረት እናድርግ ሲሉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም